top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

እኔ አንችን ስጠላሽ! (ከገብረክርስቶስ ደስታ ‹እኔ አንችን ስወድሽ› ግጥም ሙሉ አፃፃፉ ተወስዶ መልእክቱ



ሁለት አስርት አመት ብዙ ሺህ ዘመናት እልፍ አመት መሰለኝ ፍቅሬ አንችን ስጠላሽ ቀኑ ረዘመብኝ! ደመኛ አይኖችሽን በጥላቻ እያየሁ ምየ ተገዝቸ ውዴ እጠላሻለሁ !!

እኔ አንችን ስጠላሽ …. እንዳባቴ ገዳይ እንደደመኛየ

እንደክፉ ቀን ቃል እንደ ቀን ስቃየ እንዳገር አስገንጣይ እንደታሪክ አፍራሽ በህዝቦች መካከል የቂም ቁርሾ ቀስቃሽ በአርባ ክንድ ምላስ አርባ አመት ሊወዘፍ ዙፋን የሚጠግን ራሱን የሚያገዝፍ እንዲያ ነው ምጠላሽ !!

እኔ አንችን ስጠላሽ ድርጊቱ እንደሞተ ቃሉን እያንኳኳ እንዳገሬ ካድሬ ደረቅ ፖለቲካ እንደአዲስ አበባ የመንገድ ዳር ሽታ ሽቅብ ቁልቁል ንጦ ከአልጋ እንደሚጥል እንዳተት በሽታ እንዳገሬ ውሃ እንደዱርየ ልጅ በሳምት አንድየ ቤት እንደሚመጣ እንዳገሬ መብራት ጨለማ ደግፍ መግለጫ ሚያወጣ እንዲያ ነው ምጠላሽ !

እኔ አንችን ስጠላሽ . . . እኔ እኔ እንደሚል እንደ ዘረኛ ሰው ዘሩን ሲያንዘረዝር በዘረኛ ቀንበር አገር እንደሚያርሰው ከኔ ወዲያ ላሳር እንደሚል አጋሰስ ተላምጦ እንደተፉት እንደከበት ሞላሰስ

እኔ አንችን ስጠላሽ . . . . ተቃወሙኝ ብሎ በየመንገዱ ዳር አጥንት እንደሚሰብር ደም እንደሚቀዳ ነብስ እንደሚነጥቅ የትውልድ እዳ ! በራሱ ወገን ላይ ሰይፍ እንደሚመዝዝ ደም የጠማው አራጅ ራሱን አዋርዶ በአለም ህዝቦች ፊት አገርን አዋራጅ እንደስር ካቴና እንደድራማ ክስ እንደ “ዶክሜንታሪ” ባፉ እንደሚያድር ባንዳ ተብለጥልጦ አዳሪ እንደውሸት ዜና እንዳተት ኮተቱ እላይ ተቀምጦ በደሃ ህዝብ ላይ ሞት እንደሚያዝ ገልቱ

እኔ አንችን ስጠላሽ . . . የደሃ አደጉን ቤት በትቢት አፍርሶ ቦርጭ እንደሚያደልብ ቦታ እየሸቀጠ ትውልድ እንደሚገድል በየመንበሩ ላይ ጋብቻ አማችቻ ሽል እያስቀመጠ በወታደር ጫማ ፍትህን ረግጦ የህዝቡን አደራ ሳያላምጥ ውጦ ዋላችሁ እንደሚል እግሩን አንፈራጦ እንዳምባ ገነን ጅል …. ብልጥ ከኔ በላይ እንደሚል ናዚላ ህዝቡ ጠግቧል የሚል ህዝቡን እየበላ እንደቂል ዘማሪ ሁልጊዜ አበባየ እንደሚል ሞዛቂ የህዝብን አንጡራ በግፈኛ መዳፍ ጧት ማታ ሞልቃቂ

እኔ አንችን ስጠላሽ . . . ብቻ ምን ለበልሽ ምድር ይጠበኛል ሰማይ ይቀርበኛል እጠላበት መጠን ጥላቻ ያንሰኛል ! ብቻ ምን ልበልሽ በዘመኔ ሁሉ እልፍ አጋንቶች በወሬ ሰምቸ በአይኔ አይቻለሁ ግን አንችን ሳስብሽ ካጋንቶች በላይ አጋንንት በሆነ ልቤ እጠላሻለሁ !


26 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page