top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የዘቢዳር ውበት ቡታጅራይከፋኛል እንዳትነኳት፣

የእውቀት አባቴ እናቴ ናት፣

ምሳሌ ናት ለመደመር በአንድነት፣

ይከፋኛል፣አታስከፉዋት።

ከፋሽ ሲሉኝ ከፋኝ፣

የማደርገው ጠፋኝ።

የፍቅር አድባሯ፣የዘቢደሯ ፈርጥ

ላያት ሁሉ የምትማርክ፣

ሳትሰስት ፍቅር የምትሰጥ።

ከዘቢደር የገዘፈ፣

ህልውናሽን ያገዘ፣

ባፍቃሪሽ ልብ የተፃፈ፣

ላንቺነትሽ የሚመጥን፣

ስም ያውጡልሽ የማይለወጥ

ብለው ይጥሩሽ የፍቅር ፈርጥ።

የዘቢደር ውበት፣የዘቢደር ጥጉ፣

ባንቺ ና በህዝብሽ ነው፣የሚዘከረው ወጉ።

ከድሮም አውቀሽው፣የትልቅነትን ጣራ፣

ሳትታጠሪ በዘመኑ ልክፍት፣በጎሳ ቆጠራ፣

ሳትይ መስቃን፣ ሳትይዶቢ

ልብ ሰጥተሽ ለወጪ ገቢ

ሳትይ ትግራይ፣ይህ ኦሮሞ ይህ አማራ፣

በማንነትሽ የኖርሽዋ ፣በፍቅርሽ ዳራ፣

ሰላምሽን ያብዛው፣ውዷ ቡታጅራ።

የተኝቢ ብሎ መስቃን፣የብሳቢ ብሎ ሶዶ፣

እንግዳውን ተቀብሎ፣ከልብ ወዶ፣

ኖሯል ህዝብሽ፣ ክፋት ክዶ።

የምጠብኝን ተቀብሎ፣

ባህል ቋንቋ ተቀባብሎ፣

ወለኔ ስልጤ በአንድ አዝሎ፣

ኖሮብሻል ህዝብ፣ልዩነትን ጥሎ።

ጡመን ብሎ ከማረቆ፣

እውነት አውቆ፣

ወሬ ንቆ፣

ተቻችሎ ተከባብሮ፣

ደጉ ህዝብሽ ኖሮብሻል ፣ጥልን ርቆ።

የተጣለ ፣የተገፋ፣

የጠፋበት ወይ ያጠፋ፣

ባገር ባህል ባገር ዳኛ፣

በፈረዝገኜ በኛው ለኛ፣

ዘር ሀይማኖት ሳይለያይ፣

ፊት ለፊት ፍርድን የሚያይ፣

ሰላምሽን አስጠበቋል ሆኖ ከላይ።

ቡታጀራ ምን ጎደለ ሁሉ ሞላ፣

ሰውነህና ብትጋጭ፣ብትጣለ፣

ሰው አጥፍተህ፣ደም ብትቀባ፣

ዘመድ ባይኖርህ አትባባ፣

ፈርዘገኜ ቤት ፣ ቶሎ ግባ።

ታገኛለህ ፍትህ እዛ፣

ጉቦ አልባ ያልተንዛዛ።

ተብሎልሽ በዙሪያሽ ህዝብ

ቡቴ እኮ ነሽ የፍትህ ዘብ

ቡታጅራ፣

የፍቅር ዳራ፣

ፍቅርን ለተራበ ያጠገብሽ ቀዬ፣

በእውቀት የተጠማን ያረካሽ ቀዬ፣

ከፍቷታል ሲሉኝ ልመን እንድት ብዬ።

ከፋሽ ሲሉኝ ከፋኝ፣

የምሆነው ጠፋኝ።

ከእውቀት መዕድሽ የቀሰመ፣

አንቺን ሲያምሽ የልታመመ፣

በሽታኛ ነው፣ያልታከመ፣

ሀኪም ሆኖ ካሳመመሽ፣

ውለታቢስ ከሆነብሽ፣

ያገኘዋል፣ሳይውል ሳይመሽ።

የዜሮ አራት እናቶች ፣ቂጣ ጋግረው የቀለቡን

በፍቅር፣ በምግብ ፣በአብሮነት ያጠገቡን

እንባቸው ይፋረደው፣ይፀፅተው አሁን አሁን።

እባካችሁ አትንኳት ፣አለብኝ ውለታ፣

በውስጤ የቀረ፣አለብኝ ትዝታ፣

የእናቶቿ ፍቅር ፣ልዩው ሀሙስ ማታ፣

የቡላ፣የአይቤ፣ የቡና፣የእጣኑ ሽታ፣

የማንዙማ ዜማ፣የሚፈጥረው ደስታ፣

የተሟሟቀው ሀድራ፣የለሌው ጫጫታ፣

አርብን የሚጠብቁ፣የልጆች ጫወታ፣

ውስጤ ይሰማኛል አለብኝ ትዝታ።

እፁብ ደንቅ ያደረጋት፣ከህዝቧ ተደምሮ፣

ቡታጀራ አለት፣የሚያምር ተፈጥሮ፣

ጋልበን የማንዘልቀው በትዝታ ፈረስ፣

እነ እሬሻ፣የኢሪንዛፍ ወንዝ፣

ማማሩ ለጉድ ነው ረጋ ብሎ ሲፈስ።

ልብስ ስናጥብበት፣ስንታጠብ ገላ፣

ቆሻሻችን ወስዶ፣እኛን እያጣራ፣

ሰው አደረገን ቆሻሻ ሚጠላ።

ፍሬፍሬው ለይነጥፍ ፣ክረምት በጋ፣

ወንዞችን ቸራት፣ድንቅ ፀጋ ።

ቡታጅራ ፣ወንዛ ወንዙ፣

በህለ ብዙ በዓለ ብዙ፣

ባንቺ ፍቅር የተያዙ፣

ጠላትሽን ይጠላሉ፣

በክፋትሽ ይከፋሉ።

የኔ ብጤ የደከሙ፣

ህመምሽን ሲሰሙ፣

ይምጣሉ ቃል ሊገጥሙ።

ቡታጀራ ወንዛ ወንዙ

በህለ ብዙ፣በዓለ ብዙ

ሊቃእ፣መውሊድ፣ሱሙት ሰንጋ፣

ህብረ ብሄርን፣ያጠጋጋ፣

ሰላምሽን ያረጋጋ፣

ባህል አለሽ፣በዓል አለሽ፣

የደባረ፣ያለው ዋጋ።

መስጂድ ቤተክርሲቲያን፣ተጠጋግተው፣

አንዱ ካንዱ፣ተከባብራው፣

አዛን ቅዳሴውን፣አሰምተው፣

አማኙንም ባንድ አስማምተው፣

አኑረዋል አኑረሻል፣ሳይከፋቸው።

ቢከፋሽም ተጋይው ያን ተራራ፣

አንዴስሚኝ ቡታጅራ፣

እጅ አትስጪ፣ልብሽ ቢደማ፣

ፈተናው ነው ወቅቱ ፍቅር ለሚያለማ፣

ያልፋል አይዞሽ ይህ ጨለማ።

የህመምሽ መንስኤ የያዘሽ በሽታ፣

ከየት ብሎም ከየትም ይምጣ፣

አይገባሽምና ቶሎ ለቆሽ ይውጣ።

ቡታጅራ ባለወለታዬ ክፋሽን አያሰማኝ

አላህ ሀገራችንንም ሆነ ዙሪያችንን ሰላም ያድርገው።

በሸምሱ ሱልጣን


105 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page