top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

እስከ ካርሙጆ - ክፍል 1(ማስታወሻነቱ በለዛ ጫወታው ለማረከኝ የሀመር ወጣት ፣ አይኬ ኦይታ)

ተራሮች አሉ፡፡ ተራሮቹ ቁጥቋጧማ ዛፎች ለብሰዋል፡፡ ዛፎቹ ከፍ ካለ አየር ፀባይ ጋር ፍቅር እንዳላቸው የዝግባ ዛፍ ቁመታቸውን ወደ ሰማይ ያንጠራሩ አይደሉም ፡፡ እንደዋርካ ዛፎች ብዙ ቁጥር ያላቸው እጆቻቸውን ወደጎን የዘረጉም አይደሉም፡፡ የሚታዩትን በርካታ የዛፍ አይነቶች በስምም ይሁን በቡድን በቡድን አርጎ ለመጥራት የመስኩ ተመራማሪ መሆን ያሻል፡፡

ተራሮች አሉ፡፡ ተራሮቹ የጠቀስኳቸውን የዛፍ አይነቶች ለብሰዋል፡፡ ፀጥ ያሉ ናቸው፡፡ አሻቅቦ የሚያይ ሰው የቁጥቋጦ ስጋ በለበሰው ክፍላቸው መካከል ትንሽ ደም የለሽ የተራራ አጥንቶችን ይመለከታል፡፡ የሆነ ትልቅ የተፈጥሮ ሀይል፣ በገዘፈ እጅ አንስቶ በተወረወረ ቁስ ስጋቸውን አራግፎ፣ ደማቸውንም አንጠፍጥፎ በአጥንታቸው እንደተዋቸው ሁሉ፡፡ ስጋ ለባሹ አካልና ይኸው ጠባሳማ አካላቸው በአንድነት ሆኖ በዝምታ፣ በዝምታ ላይ ታላቅ ግርማ ደርበው ፣ እንደሰው ሁሉ ዓይኖቻቸውን ተክለው ፣ ባሻገር የሚገኘውን ዝም ያለ እጅግ ሰፊ የሆነ ሜዳማ ደን፣ ደኑን አልፎ ባሻገር የሚገኙ ተራሮችን የሚመለከቱ ይመስላሉ፡፡

እዚህ ግርግርና ሁከት የለም፡፡ እዚህ እሩጫ፣ የሩጫ እግሮች የፈጠሯቸው እረፍት የሚነሱ መንኮሻኮሾች እና አርምሞ የሚከለክሉ፣ የሰከነን መንፈስ የሚያማስሉ፣ የሚያደፈርሱ ነገሮች የሉም፡፡

እርግጥ ነው፡፡ አልፎ አልፎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ከብቶች፣ በመንጋ የተሰማሩ ፍየሎች ይታያሉ፡፡ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር እረኞቻቸው ከመንጋዎቹ ፊት ወይም በኋላ ሆነው አይታዩም፡፡ ግራና ቀኝ በሚገኙት ጥቅጥቅ የበረሀ አረንጓዴ ደኖች ውስጥ፣ ከሰው ዕይታ ተሰውረው ተቀምጠዋል፡፡ አናት ፈንክቶ የሚገባውን ሙቀት ለመሸሽ አስበው የመረጡት ዛፍ ጥላ ስር በርኩማቸውን ተንተርሰው ጋደም ብለው ይሆናል፡፡ እንደዚያ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ለዕንቅልፍ እጅ ሳይሰጡ፣ አይኖቻቸውን ለሰመመን እንቅልፍ ከድነዋል፡፡ በሰመመን ውስጥ ሆነው ዙሪያ ገባቸውን በእዝነ ልቦናቸው ያዳምጣሉ፡፡ ዙሪያ ገባቸውን በእዝነ ህሊናቸው ይመለከታሉ፡፡ የፍየሎቻቸውንና የበጎቻቸውን፣ የከብቶቻቸውን እንቅስቃሴዎችና ሌሎች ተግባራት ያዳምጣሉ፡፡ ያሸታሉ፡፡

የፍየሎቻቸው ቀለማት ደማቅ እና የሚስብ ነው፡፡ አንዱ ፍየል ላይ ብቻ የተለያዩ ቀለማት ህብር ፈጥረው ሲታዩ የፈጣሪ ዕጆች ካልሆኑ በቀር የሰው ልጅ ፎቶ ኮፒ የሚያደርጋቸው ዓይነት ዐይደሉም፡፡ የቀለም ቅቡ ብቻ ሳይሆን፣ ቀለም ተቀብቶ በቫርኒሽ የተወለወለ ይመስል ቆዳቸው ያንፀባርቃል፡፡

ይህ በአንድ ላይ የሚታየው ዥንጉርጉር ውብ ቀለም፣ ዥንጉርጉር የተፈጥሮ አይነት በፀማዮችም፣በበናዎችም ፣በሀመሮችም በኛንጋቶሞችም ላይ ይገለጣል፡፡ ሁሉም ከእንስሶቻቸው በተወረሱ ደማቅ ቀለማት ህብር ጨሌዎች፣ የአፈር ዓይነቶች ፣ደማቅ ቀለማት ባላቸው ልብሶች ማጌጥ ነፍሳቸው ናት፡፡


21 views0 comments
bottom of page