top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የፍርሃት አባዜ የተጠናወታቸው በህክምና ይፈወሳሉከአለም ህዝብ ከ10 በመቶ በላይ የፎቢያ ተጠቂ ነው::

ሴቶች ከወንዶች ሁለት እጥፍ ያህል በፎቢያ ይጠቃሉ::

ከፍ ያሉ ሥፍራዎችን የመፍራት ችግር (ፎቢያ) እንዳለበት ያወቀው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ የመማሪያ ክፍላቸው ወደሚገኝበት 3ኛ ፎቅ ለመሄድ ገና ደረጃዎችን መውጣት ሲጀምር ሰውነቱ ይንቀጠቀጣል፣ ልቡ በሃይል ይመታል፣ ፍርሃት ፍርሃት ይለዋል። ይህ ነገር በጊዜ ሒደት ሊተወው እንደሚችል ቤተሰቦቹም ሆኑ ጓደኞቹ ቢነግሩትም እሱ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እየባሰበትና ለከፍታ ቦታዎች ያለው ፍራቻ እየጨመረ ሄደ፡፡ እጅግ በበዛ ችግርና ፈተና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ቆይታውም በበርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች የተሞላ ነበር፡፡ የመማሪያ ክፍሎቹ በህንፃዎች ፎቅ ላይ መሆናቸው በየዕለቱ በትምህርት ገበታው ላይ እንዳይገኝና ትምህርቱን በአግባቡ እንዳይከታተል እንቅፋት ሆነውበታል፡፡ ፍርሃቱ እጅግ የበዛ ቀን ሲቀር፣ ከመምህራኖቹ የሚደርስበት ተከታታይ ማስጠንቀቂያ ሲያደፋፍረውና እንደምንም አይኑን ጨፍኖ ወደ ክፍሉ ሲገባ የአራት አመታት የዩኒቨሲቲው ትምህርት አልቆ ወጣ፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም የአይቲ ዲፓርትመንት ክፍል የተቀጠረው ከዩኒቨርሲቲው ከወጣ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር፡፡ በተማረው ሙያና በሚወደው የሥራ መስክ መሰማራቱ እጅግ ቢያስደስተውም ያ ከልጅነቱ ጀምሮ ፈተና የሆነበት ልክ ያጣ የከፍታ ፍራቻ እዚህም ተከትሎት መጣ፡፡ ወደ ቢሮው ለመሄድ ገና ከቤቱ ሲወጣ ሃሣብ የሚሆንበት ባለስምንት ደረጃዎቹን ፎቅ መውጣት ነበር፡፡ ቢሮው የሚገኘው እጅግ ዘመናዊ አሳንሰር ከተገጠመላቸው የከተማዋ አዳዲስ ህንፃናዎች በአንዱ ላይ በመሆኑ ሊፍት የመጠቀም ዕድል ቢኖረውም ለአንዲትም ቀን ሞክሮት አያውቅም። “ሊፍት ውስጥ ገብቼ በህይወት የምወጣ አይመስለኝም፡፡ የሊፍቱ በር ጭርሱኑ የሚከፈት ሁሉ አይመስለኝም፡፡ በደረጃ ስወጣ እንኳን ዘወር ብዬ የመጣሁበትን ደረጃ ወደኋላ ማየት አልችልም፡፡ ህንፃው መስታወት በመስታወት ሆኖ ደረጃ እየወጣሁ መሬቱን ቁልቁል የማየው ከሆነ አዙሮኝ ልወድቅ ሁሉ እችላለሁ፡፡ በህይወቴ እንደፎቅና ሊፍት የምጠላው ነገር የለኝም፡፡ ይህ የፎቅና የደረጃ ፍራቻዬ ለትምህርቴም ለሥራዬም መሰናከል ሆኖብኛል፡፡ ትምህርቴን ለመቀጠል ወይም ደግሞ ሥራዬን ለመቀየር ፍላጐቱ ቢኖረኝም ይኸው ችግሬ እንደሚከተለኝ ስለማወቅ መድፈር አቅቶኛል፡፡ ይህንን ችግሬን ለማስወገድ የተለያዩ ሙከራዎችን ባደርግም አልተሳካልኝም፡፡ ሁሉም ቀስ እያለ ይተውሃል ይሉኛል፡፡ ይሄው 36 ዓመቴን አጠናቅቄአለሁ፡፡ መቼ እንደሚተወኝ አይገባኝ። በአውሮፕላን መብረር ስለማልችል በርካታ ስልጠናዎችና ልዩ ልዩ የውጭ አገር ዕድሎችን አጥቻለሁ፡፡ ችግሩ ካለበት ሰው ሌላ ማንም ስሜትሽን በቅጡ ሊረዳሽ አይችልም፣ ነገሩ ችግር ብቻ ሳይሆን በሽታም ነው፡፡ ሐኪም የማያድንሽ፣ ሰው የማያዝንልሽ በሽታ!” ይህንን ያለኝ በኢትዮ ቴሌኮም የአይቲ ዲፓርትመንት ክፍል በኃላፊነት ደረጃ ላይ ተመድቦ የሚሰራ አንድ ወጣት ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የተጠናወተው ከፍታ ቦታዎችን የመፍራት አባዜ (አክሮ ፎቢያ) ዕድሜው የወጣትነትን ድንበር እስኪሻገር ድረስም አልተወውም፡፡ ከልክ ያለፈ፣የተጋነነና ተጨባጭ የሆነ ምክንያት በሌለው ጉዳይ የሚፈጠር ስር የሰደደ ፍርሃት ፎቢያ ይባላል፡፡ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በዚህ ችግር የመጠቃት ዕድላቸው በሁለት እጥፍ እንደሚጨምር በእንግሊዝ ተመራማሪዎች የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከዓለማችን ህዝቦች 10 በመቶ ያህሉ በአንድ የፎቢያ ዓይነት የመያዝ ዕድል እንደሚያጋጥማቸው የሚጠቁመው እ.ኤ.አ በ2012 የተደረገው ይኸው ጥናት፤ በተለይም ባደጉት አገራት ህዝቦች ላይ ጎልቶ እንደሚታይ አመልክቷል፡፡ ፍርሃት ሰዎች ራሳቸውን ከተለያዩ አደጋዎች እንዲጠብቁና ከችግሩ ለመከላከል የሚያስችላቸው ፈጣን ውሳኔ እንዲተገብሩ የሚያስጠነቅቅ ጤናማ ስሜት ሲሆን ከሰው ሰው በተለያዩ ሁኔታዎችና ደረጃዎች ሊገለፅ ይችላል፡፡ ይሄ ስሜት ጠንቃቃ እንድንሆንም ያግዘናል፡፡ ፎቢያ የሚሆነው ከጤናማው የፍርሃት መገለጫ በተለየ ያለአንዳች ምክንያት የሚከሰትና ቅጥ ያጣ ጭንቀትና መረበሽን የሚያስከትል ሲሆን ነው፡፡ ልዩ ልዩ ነገሮችን ያለምክንያት ከልክ በላይ የመፍራት አባዜ (ፎቢያ) በአራት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሚከፈል የገለፀው ጥናቱ፤እነዚህም የደም ፍራቻ፣ የተፈጥሮ ሁኔታዎች ፍራቻ፣ የእንስሳት ፍራቻና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ፍራቻ እንደሚባሉም ጠቅሷል፡፡ ፎቢያ መነሻው ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ምክንያት እንደሌለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የሥነ ልቦና ባለሙያው ዶ/ር ተከተል ካሳሁን ይህንኑ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “የፎቢያ መነሻና ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው በግልፅ የሚቀመጡ ነገሮች የሉም፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ወደ ፎቢያነት ደረጃ ከመድረሱ በፊት የሚኖር ተራ ፍርሃት አለ፡፡ ለዚህ ፍርሃት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶች ደግሞ ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ – አንድ በልጅነቱ ሰው ከከፍታ ላይ ወይም ከፎቅ ላይ ተወርውሮ ሲወድቅ ያየ ሰው፣ ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ ለከፍታ ቦታዎች የሚኖረው ፍራቻ እያደገ ይሄድና ወደ ፎቢያ በመለወጥ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን አደጋ ላይ ሊጥልበት ይችላል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ፎቢያ ደግሞ ያለምንም ጥርጥር የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል” ብለዋል፡፡ በጣም የተለመዱና የበርካታ ሰዎች ችግር ከሆኑት ፎቢያዎች መካከል የከፍታ፣ የጨለማና የውሃ፣ ድልድይ የመሻገር፣ ፎቅ ላይ የመውጣት፣ በአውሮፕላን የመሳፈር፣ መኪና የመንዳት፣ ዳገታማ ቦታዎች ላይ (ፎቅ) ላይ የመውጣት፣ በሊፍት (በአሳንስር) የመሳፈር፣ መሰላል ላይ የመውጣትና ሰዎች በተሰበሰቡባቸው ቦታዎች ላይ የመገኘት ፎቢያዎች ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከፍታን የመፍራት ፎቢያ (አክሮፎቢያ) ይህ አይነቱ ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ዳገታማ ቦታዎች ላይ፣ ፎቅና መሰላል ላይ እንዲሁም ደረጃዎች ላይ መውጣትን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ በሊፍት (በአሳንሰር) መውጣትና መውረድ ለእነዚህ አይነት ሰዎች የሞት ያህል አስፈሪ ነው፡፡ የከፍታ ፍራቻ ያለባቸው ሰዎች፣ በአውሮፕላን መሳፈርን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ የዚህ ፎቢ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ድልድይ መሻገርንና መኪና ማሽከርከርንም ይፈራሉ፡፡ ፍራቻው በአብዛኛው የፎቢያ ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን ችግሩ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን በማወክ በተጠቂው ላይ ስነልቦናዊ ቀውስን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የደም ፍራቻ (ሄማቶፎቢያ) የዚህ ዓይነት ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ደምን ጨምሮ ማናቸውንም ከደም ጋር ንኪኪ ያላቸውን ነገሮች የማየት ከፍተኛ ፍራቻ አለባቸው፡፡ መርፌ፣ ምላጭና የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ለእነዚህ ሰዎች ፍራቻ መነሻ ሊሆኗቸው ይችላሉ፡፡ ደም ባልሆነና ደም ሊሆን ይችላል ባሉት ነገር ሁሉ ፍርሃትና ድንጋጤ ይፈጠርባቸዋል፡፡ የማህበራዊ እንቅስቃሴ ፍራቻ (ሶሻልፎቢያ) ይህ አይነቱ ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው ሥፍራዎች ላይ መገኘትን አጥብቀው ይፈራሉ። በሰዎች ፊት መብላት፣ መጠጣትና መናገርን ፈጽመው አይደፍሩም። ምክንያታቸው ደግሞ በሥፍራው የተሰበሰቡት ሰዎች ስለነሱ የሚያወሩ ስለሚመስላቸው ነው። ይህ አይነቱ ጥልቅ ፍርሃት የሰዎችን ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚገድብና ከፍተኛ የሥነልቡና ችግር የሚያስከትል እንደሆነ የሥነ-ልቡና ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ የዚህ ችግር ተጠቂዎች እንደሠርግ፣ ለቅሶ፣ ግብዣ፣ ሃይማኖታዊ በአላት በሚከበሩባቸው ሥፍራዎችና ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ላይ ጨርሶ መገኘት አይፈልጉም፡፡ ደህንነት የሚሰማቸው በፀጥታ ሥፍራ ብቻቸውን ሲሆኑ ነው፡፡ የእንስሳት ፎቢያ በሰው ልጅ ላይ ምንም ጉዳት የማያደርሱ ወይንም የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ አነስተኛ የሆኑ እንስሳትን ጨምሮ ለማንኛውም እንስሳ ጥልቅ ፍራቻ ያድርባቸዋል – የዚህ ችግር ተጠቂዎች። ውሻ፣ ድመት፣ አይጥ፣ ሸረሪትና ጉንዳን እጅግ የሚያስፈሯቸው ሲሆን እነዚህን እንስሳት በተመለከቱ ጊዜ ወይንም በሌሉበት ሥፍራ ስማቸው ሲነሳ ከፍተኛ ፍርሃት ይሰማቸዋል፡፡ ይህ ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች በአብዛኛው ለችግሩ መነሻ የሆኑ ምክንያቶች ይኖሯቸዋል፡፡ በልጅነታቸው በእንስሳ የመነከስ ወይም ሌሎች ጉዳቶችን የሚያደርስ አደጋ ከገጠማቸው እስከ ዕድሜያቸው ፍፃሜ ድረስ እነዚህን እንስሳት ሲፈሩና ሲሸሹ ይኖራሉ፡፡ የጨለማና የውሃ ፎቢያ የዚህ ፎቢያ ተጠቂዎች ለጨለማ ወይንም ለውሃ ያላቸው ፍራቻ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ብርሃን በሌለባቸው ቦታዎች ላይ መንቀሳቀስም ሆነ ጨለማ በሆኑ ሥፍራዎች ላይ መገኘትን ፈፅመው ይፈራሉ። የጨለማ ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች፣ በአብዛኛው የከባድ ራስ ምታት ተጠቂዎች ናቸው፡፡ የውሃ ፎቢያ ተጠቂዎችም በተለይ ብቻቸውን ሆነው ውሃ ባሉባቸው አካባቢዎች መዘዋወርን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ አነስተኛ ኩሬዎች ወይንም የውሃ መውረጃዎች ለእነዚህ ሰዎች ፍርሀት መነሻዎች ናቸው፡፡ ችግሩ ባስ ያለባቸው ሰዎች ደግሞ ለብቻቸው ሰውነታቸውን መታጠብም ሆነ ዋና መዋኘት ፈፅመው አይደፍሩም፡፡ የፎቢያ ተጠቂነት በምን ይገለፃል? አንድ ሰው የፎቢያ ተጠቂ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሰውየው ለነገሮች እጅግ የተጋነነ እና ቅጥ ያጣ የፍርሀት ስሜትን የሚያሳይ፣ ስሜቱ በእጅጉ የሚረበሽ፣ ውጥረት የሚያጠቃው፣ እንዲሁም ከሥፍራው ለመራቅ ወይም ለመሸሽ ጥረት የሚያደርግ ከሆነ የፎቢያ ተጠቂ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ የፎቢያ ችግር በህክምና ሊድን ይችላል? የፎቢያ ችግር በህክምና እርዳታ ሊድን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ግን ራሱ የፎቢያ ተጠቂው ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አንድ የፎቢያ ተጠቂ የሆነ ሰው ችግሩን የሚፈጥርበትን ነገር እንዲጋፈጠውና ውስጣዊ የፍርሃት ስሜቱን በማስወገድ፣ ፍርሀቱ ምክንያታዊ መሆን አለመሆኑን አጥብቆ መጠየቅና ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ የከፍታ ፍራቻ ያለበት ሰው፣ ሌሎች በደረጃዎችም ሆነ በአሳንሰር (ሊፍት) በመጓዛቸው ምክንያት የገጠማቸው ችግር አለመኖሩን በማየት፣ አዕምሮው ለፍርሃቱ ምላሽ እንዲሰጥና ጉዳዩ ምንም ችግር እንደማያስከትልበት እንዲነግረው ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ የችግሩ ተጠቂ ከነገሮች ጋር ቀስ በቀስ እንዲላመድና በውስጡ ያለው የፍርሃት ስሜት በሂደት እንዲወገድ ለማድረግ ያስችለዋል፡፡ ስር የሰደደና በራሱ በችግሩ ተጠቂ ጥረት ሊወገድ ያልቻለውን የፎቢያ አይነት ለማስወገድ የሚረዳ “ኮግኒቲቭ ቢሔቨየራል ቴራፒ” የሚባል የህክምና ዘዴ ያለ ሲሆን ህክምናው የሚሰጠው በስነ-ልቦና ባለሙያዎች ነው፡፡

============

የፍራቻ (ፎቢያ) ዓይነቶች

የመብረቅ ፍራቻ – አስትራፎቢያ የማስመለስ ፍራቻ – ኢሜቶፎቢያ የወሲብ ፍራቻ – ጂኖፎቢያ የብቸኝነት ፍራቻ – ሞኖፎቢያ የአይጥ ፍራቻ – ሙሶፎቢያ የጭለማ ፍራቻ – ኒክቶፎቢያ የቁጥር ፍራቻ – ኒውሮፎቢያ የእባብ ፍራቻ – ኦፊዲዮፎቢያ የእሳት ፍራቻ – ፓይሮፎቢያ የሞት ፍራቻ- ታናቶፎቢያ የባቡር ፍራቻ – ሲዴሮድሮሞፎቢያ የፀጉር ፍራቻ – ትሪቾፎቢያ የመርፌ መወጋት ፍራቻ – ትራይፓኖፎቢያ

Source-.addisadmassnews


37 views0 comments
bottom of page