top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"እንብላ! እንደምንለው ሁሉ እንስራ!" ብንል ኖሮ የት እንደርስ ነበር? (ክፍል- 01)



በባህላችን እንብላ ማለት አመጣጡ ከመተሳሰብ ወይስ ከማጣትና ከችጋር መሆኑን አላውቅም። ሆኖም ግን አንድ ምግብ ብቻ ይዞ ለማይጠቅም ነገር የሚወጣውንና የሚገባውን ካንገት በላይ እንብላ ማለት ማስመሰል ነው። ለነገሩ የተለመደ ስለሆነ እንጂ እንብላ የተባለ ሁሉ አይበላም። ታዲያ ይቺን አባባል ያሻሻልኩ መስሎኝ አንድ ወቅት ላይ ዝም ከማለት ቅመስ/ቅመሺ ማለት ጀመርኩ። አንድ ምግብ ይዞ እንብላ እንብላ እያሉ ከማስመሰል ቅመሱ ማለት ይሻለል መስሎኝ። አባባሉ እንግዳ ቢሆንም አሁንም ያው ነኝ።

የደረሰብኝን ልንገራችሁ። ከእለታት አንድ ቀን አንዷ ስበላ ስለደረሰች፤ እኔ፤ "ቅመሺ" እሷ፤ "ምን?" አለችኝ። እኔ፤ ያልሰማችኝ መስሎኝ ደግሜ "ቅመሺ" አልኳት፤ እምበላውን እንዲትቀምስልኝ ፈገግ እያልኩ። እሷ፤ እንደ መጠየፍ ቃጣትና አባባሉ ስለደበራት መሰለኝ " እ ይ ይ ይ ይ እሱስ ይቅርብኝ" ብላኝ አለፈች። እኔ በሃሳቤ፤ "ይቺ ሴትዮ ምን ነካት? አለባበሴ ነው ወይስ አጠያያቄ እንዲህ የደበራት? ምናልባት እየበላሁ ፈገግ ስል ጥርሴ ላይ ምግብ አይታ ይሆን?" እኔ እንጃ።

አንዳንድ ጊዜ ከባህሉ መውጣት አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶቻችን የማናምንበት ነገር ግን ብዙ ሰወች ደግሞ እራሳቸውን የሚሸነግሉበት ባህልና ልምድ አለን። የባህል ምግባችን ደግሞ በእጅ ስለሚበላ አንዳንዱ ሰው እጁን ሳይታጠብ እንጀራና ወጡ ላይ ዝፍቅ ይልበታል። ያም ሆነ ይህ አንድ ምግብ ይዞ እንብላ ማለት ሰወችን መሸንገል ስለመሰለኝ አንዳንድ ጊዜ ዝም እላለሁ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ለምሳሌ ለሰላምታ በጣም ከቀረቡኝ ቅመሱ ማለቴ አልቀረም።

ያሁኑን አላውቅም እንጂ ዱሮማ ሞሰቡ እንዳይታ ምግብ በላይ በላዩ ላይ ይጨመራል። በኔ አስተያየት ምግብና ስራ ማስተረፍ ነውርና ስንፍና ነው። ሰራተኛ ይበላዋልም ይባላል። ምግብ ቢተርፍም ልጆች ይበሉታል ይባላል። ለመሆኑ ልጆች ለምን ትራፊ ይበላሉ? በኋላ ሲያድጉ ለማኝ እንዲሆኑ? በራሳቸው እንዳይተማመኑ? አንዱ አይነት ጭቆና ከዛ ነው እሚጀምረው። አዋቂው ለምን ለራሱ መጥኖ አያቀርብም? ለልጆችስ በትራፊ ፋንታ ለምን ተመጥኖ አዲስ ምግብ አይሰጣቸውም?

ግዳጁም እንደዛው ነው! አንዱ በቃኝ ወይም ጠገብኩ ሲል ........ እንዴ! አረ እባክህ ብላ እያሉ ማስገደድ። ይህ ደግሞ የሚያሳየው ተነግሮን የማንሰማና የማይገባን ይመስላል። አንዳንድ ጊዜም "በቃኝ ሳይሆን ጠገብኩ ነው ያልኩት" ሲሏቸው የማይሰሙ አሉ። አይ ግደለም ትንሽ ጨምር፣ በሞቴ! ማድ ላይ ያለው ፍቅራችን ብዙ ነው። ግን የሚታይ፣ የሚያዝና የሚጨበጥ ፍቅር አይመስለኝም። እንዲሁ ዝም ብለን የማያስፈልግ ቦታ ላይ የምንጠቀምበት ፍቅር ቀልድ ይመስላል። ለመስራት ቢሆን ኖሮ ታሪኩ ሌላ ነው።

ነገሩን ያነሳሁት እንብላ ማለት ትክክል ነው ወይስ አይደለም ለማለት አልደፍርም። ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን የምንበላውን ለማካፈል ፍቃደኛ እንደመሆናችን መጠን የጋራ ሃሳብ አብሮ ለመካፈል ለምን ቸገረን? አብረን ለመብላት ፈቃደኞች እንደመሆናችን መጠን አብረን ለመስራት ለምን ቸገረን? ለጋራና ለብሄራዊ ጥቅም በአንድ ለመቆም እንዴት ቸገረን የሚሉት ጥያቄወች ስላስቸገሩኝ ነው። ተረትም አለው። ኢትዮጵያዊ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መስራት አይችልም ይባላል። ይህ አባባል ኢትዮጵያዊ ከመስራት ይልቅ መብላት ይወዳል ለማለት ይመስላል። ኢትዮጵያዊ የበለጠ ስራ ከመስራት ይልቅ መብላት የሚወድና ለመብላትም የሚያልም መሆኑን በብዙ ሰወች ላይ አይቻለሁ። ለምሳሌ ሰርግ ላይ፣ ዝግጂት ቦታ ላይና ማንኛውም አይነት ግብዢያ ላይ ብፌ ሲኖር አብዣኛውን ኢትዮጵያዊ መታዘብ በጣም ቀላል ነው። ምግቡ በነጻና ልቅ ስለሆነ ሰወች መብላት የማይችሉትን ያህል ሳህን ላይ ቆልለው የሚያወጡ ጥቂቶች አይደሉም። ያቀረቡትን ምግብ መብላት ያቅታቸዋል። በኋላ ምግቡ ይጣላል። እንዴት ሰው የሚበላውን ያህል መጥኖ አያቀርብም? ምግቡም የማይጥመው ከሆነ መጀመሪያ ጥቂት አቅርቦ በኋላ እንደሁኔታው መጥኖ ማቅረብ እንዴት ሰው ተሳነው? እኔ እንደሚመስለኝ ብዙ ኢትዮጵያዊ ያለአቅሙ ምግብ በብዛት ለመብላት ይጓጓል። ቢፌ ሲሆን ደግሞ ነጻ ስለሆነ ጉጉቱ ይብሳል። ባደጉት ሃገሮች ብዙ ምግብ ይጣላል። ይህ የሚጣል ምግብ ግን ቀኑ ሲያልፍበት፣ ሆቴሎች ወይም የምግብ መደብሮች ምግብ በጊዜው ሳይሸጥላቸው ሲቀር ወዘተ ነው።

ግለሰቦችም ቢሆኑ ምናልባት ተሰርቶ ግን ገና ሳህን ላይ ያልቀረበ ምግብ ነው የሚጥሉት። ይህ ማለት ያደጉት ሃገሮች ለምሳሌ ኖርዌይ ውስጥ ምግብ ቢበዛም ሰወች የሚበሉትን ያህል መጥነው ነው በሳህን የሚያቀርቡት። ይህ እውነት ለመሆኑ ደግሞ እኔ በየቦታውና በየሆቴሉ ልብ ብያለሁ። እነሱ ያደረጉትን አይቼ አደርጋለሁ ወይም እናድርግ ሳይሆን መመጠን መቻልን ለማንጸባረቅ ነው። እስከማስታውሰው ድረስ እኔ ሌላ ሰው ተከትየ ሳይሆን ለራሴ በቂ ምግብ መጥኜ ማቅረብ የኔ ፋንታ ነው። ለመመገብ ሳህን ላይ የማቀርበውን ምግብ መመጠን ተስኖኝ በኔ ምክንያት ምግብ መጣል የለበትም ብዬ ስለማምን ብቻ ነው። ሰው ደግሞ ምግብ ለመብላት ሲንሰፈሰፍና ስራ ላይ ደካማ ሲሆን የበለጠ ይደብራል።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ለመብላትና ለመጋበዝ የምጓጓውን ያህል ለመስራት ታታሪ ብንሆን እስካሁን የት እንደርስ ነበር? መስራት ስል ደግሞ ሁለት አይነት ስራወች ናቸው። አንደኛው የሃሳብ ስራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእንቅስቃሴ ስራ ነው። እነዚህን ሁለት አይነት ስራወች ምን እንደሆኑና ኢትዮጵያዊያን ላይ ምን አይነት ትርጉም እንዳላቸው በሚቀጥለው ጊዜ አቀርባለሁ።

ምንጭ - tatariw


23 views0 comments
bottom of page