top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው ( በላይነህ አባተ )



እንኳን ምድጃውን ሰማይን ደነቀው፣

እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው፡፡

ብረት ሲያቀልጥ ኖሮ ጭንፉር ቢል ለጊዜው፣

ጥፍት ያለ መስሎት ጭራሮ ደፈረው፡፡

ድንጋይ ሰነጣጥቆ የሚንደው ገደል፣

አድፍጦ ቢተኛ ስሙን ብሎ መቻል፣

ሊዝቀው ከጀለ ፍርክስክስ ያለ ገል፡፡

እሳት ረመጡ እሳት ነበልባሉ፣

ደካማን አይወድም ወቅትና ዘመኑ፣

ጉልቻን ገልብጠው ድፋው ባፈጢሙ፡፡

እሳት ረመጡ እሳት ነበልባሉ፣

ያልጣረን አይረዳም እንኳን ሰው እግዜሩ፣

አንተን እሚያዋጣህ መፍጀት ማቃጠሉ፡፡

ከአፈርና ውሀ ጀበና ብትሰራም፣

አፍራሹ እሳት እንጅ ገንቢው አልተባልክም፡፡

ከተፈጠርክበት እስከ ዛሬ ድረስ፣

ሊጪር የመጣን ባድ እርር ኩምትር አርገህ፣

ግዛት ድንበርህን በደንብ አስከብረህ፣

አብስላችሁ ብሉ ብለህ ስለፈቀድክ፣

ይሉኝታ ቢሶቹ ከምድጃ ጥፋ አሉህ፡፡

ስለዚህ ይቺ ዓለም ደግን ስለማትወድ፣

እምቢኝ አሻፈረኝ በልና ተውረግረግ፡፡

ጫካውና ዱሩ ጠርቶህ እንዳየኸው፣

አንበሳና ነብር ተከብሮ እሚኖረው፣

ሲነኩት ፎክሮ ስለሚዘነችር ነው፡፡

በክብርህ እንዳትኖር አንተን ሲነካኩህ፣

እንደምታውቅበት እንዳፈጣጠርህ፣

ቦግ ብለህ ተነሳ እንደ አንበሳ አግስተህ፡፡

ሆደ ሰፊ ሆነህ መፋጀት ስላቆምክ፣

በአዳቦል በጪዱ በድርቆሽ ተደፈርክ!

ትግሥትና መቻል በገል አሳፈሱህ፣

ሥራ እስከሚጀምር እሚፋጀው ክንድህ፡፡

ምሬት የለኮሰው ሰደድ እሳት ሆነህ፣

ትቢያና አመድ አርገው አጥፊህን አቃጥለህ!

እንደ ቀትር ጀንበር ስትወጣ አምርረህ፣

እንኳንስ ገለባ ውሀ አይቆም ከፊትህ!


13 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page