top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጨዋነት ምንድነው? ለመሆኑ እርስዎስ ጨዋ ነዎት?



ጨዋነት እንዴት ይገኛል? አንድ ግለሰብ ጨዋ ሊባል የሚችለው ምን ሲሆንና ምን ሲያደርግ ነው? ጨዋ ሰው ከሌሎች ጋር ምን አይነት አቀራረብ አለው? መጀመሪያ እስኪ ስለ ጨዋነት ባጭሩ እንመልከት፡፡ በኋላ ደግሞ ጨዋነትን በትንተና መልክ አቀርባለሁ፡፡ አንድ ሰው ስለ ጨዋነት ካወቀና ከተለማመደ በቀላሉ ጨዋ መሆን ይችላል፡፡ በጥቅሉና በቀላሉ ጨዋ ማለት አንድ ሰው ለመልካም አስተሳሰብና ድርጊት እራሱን ማዘዝና ስነስርአት ማስያዝ ሲቻል ነው፡፡

ለምሳሌ ጨዋ ሰው ልቡ ደግ፣ አዕምሮው ጥበበኛ ነው፡፡ በቀጠሮ ጊዜ በሰዓቱና በቦታው ይገኛል፡፡ ብዙ ከመናገር ይልቅ ሌሎችን ያዳምጣል፡፡ ሰው ሲናገር አያቋርጥም፡፡ ቅንና ትልቅ ነገር አጣምሮ ካሰበ በኋላ በተግባር ለመተርጎም ይጥራል፡፡ በስራ ያምናል፡፡ ለሚያደርገውና ለሚናገረው ነገር ሃላፊነት ይሰማዋል፡፡ ሌላ ሰው አያማም፡፡ ቂም አይዝም፡፡ የሚያናድድ ነገር ሲያጋጥመው በተቻለ መጠን እራሱን መቆጣጠር ይችላል፡፡ ወይም ንደቱ አጭርና አላፊ ነች፡፡ ስህተቱን አይክድም፡፡ ከስህተቱም ይማራል፡፡ ሲያጠፋ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ውለታ ይከፍላል፡፡ በቃሉ ይገኛል፡፡ በጥቅም አይገዛም፡፡ አስተሳሰቡና ተግባሩ ገንቢ ነው፡፡ ረጋ ብሎ ሌሎችን ሳያቋርጥ በጥሩ ቋንቋ ሃሳቡን ይገለፃል፡፡ ሃሳቡም ጠቃሚና ገንቢ ነው፡፡

በጥቅሉና በቀላሉ ጨዋ ማለት አንድ ሰው ለመልካም አስተሳሰብና ድርጊት እራሱን ማዘዝና ስነስርአት ማስያዝ ሲቻል ነው፡፡

ህይወትን የሚያያት በገንቢነቷ ነው፡፡ ለሌሎችም ተስፋና ድጋፍ ይሰጣል፡፡ በምክንያት ካልሆነ ወይም ካልተጠየቀ በስተቀር ስለራሱ ብዙ አያወራም፡፡ ሲናገርና ሲያዳምጥም አልፎ አልፎ ፈገግ ይላል፡፡ የእናቱን ቋንቋ አስተካክሎ ይናገራል፡፡ ደስታ ከውስጥ ይፈልቃል እንጂ ከውጭ በቁሳቁስና በገንዘብ ይመጣልኛል ብሎ አያምንም፡፡ መብቱንና ግዴታውን በሚገባ ስለሚያውቅና ስለሚተገብር ነጻነቱን ያስከብራል፡፡

ሰውን በደንብና ከልብ ያከብራል፡፡ ሌሎች ጥሩ ስራ ሲሰሩ ያደንቃቸዋል፥ ድጋፍም ይሰጣቸዋል፡፡ ትልቆቹንም ያከብራል፡፡ ፈገግ እያለ ሞቅ ያለ ሰላምታ ይሰጣል፡፡ ሰላምታ ሲያቀርብም ሰላም የሚለውን ግለሰብ እንጂ ጋራ ጋራውን አያይም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ጋር ሲተዋወቅ ወይም ለዕንግድነት ሄዶ እጁን ሲያስታጥቡት ብድግ ይላል፡፡ ሰው ፊትና መንገድ ላይ የግድ ካልሆነ በስተቀር ምራቁን አይተፋም፡፡ እኪሱ ውስጥ ይዞ ይጠብቃል እንጂ ብጣሽ ወረቀትም መንገድ ላይ አይጥልም፡፡ መተላለፊያ ወይም መግቢያና መውጫ ላይ ሌሎችን ያስቀድማል፡፡ ግብዢያ ላይ ለራሱ ውኋ የሚቀዳው መጨረቻ ላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ደግሞ ከብልህነት ጋር 'ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፥ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም' በሚለው ባባቶቻችን ጥቅስ ያምናል፡፡

ጨዋነት እንዴት ይገኛል?

እንግዲህ አብዛኛውን ጊዜ ጨዋነት የሚገኘው አንድ ግለሰብ ከአስተዋለ በኋላ ለተገቢው ነገር እራሱን ማዘዝ ሲችል ነው፡፡ ጥሩ ዜና ስላለኝ ልንገረዎት፡፡ ጨዋ ለመሆን ማንም ግለሰብ ሃኪም ወይም የሮኬት ሰሪና አብራሪ መሆን አያስፈልገውም፡፡ ጨዋነትም በዕድል ወይም በተፈጥሮ የሚገኝ አይደለም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ግለሰብ ጨዋ መሆን ይችላል፡፡ ጨዋነት በትምህርት፣ በልምምድ፣ በማስተዋልና ራስን ለጥሩ ተግባር በማዘዝ የሚገኝ ነው፡፡ ከተዘረዘሩት ጨዋነቶች ውስጥ እያንዳንዳችን ቢያንስ ግማሾቹን እንኳን ብንሸፍን ኢትዮጵያ አገራችን በደንብ ማደግ ትችላለች፡፡ የእያንዳንዳችንም የግል ህይወት መሻሻል ይችላል፡፡ የክብርም ባለቤቶች መሆን እንችላለን፡፡ ክብርም ሳንጠይቃት በፍጥነት ወደእኛ ትመጣለች፡፡

የተጠቀሱትን ቀላል የሆኑ ጨዋነቶችን በተግባር ስናሳይ ብቻ ነው ማደግ እምንችለው፡፡ እንግዲህ አባቶቻችን 'ነገር በምሳሌ ፥ ጠጅ በብርሌ' ብለዋል፡፡

ምንጭ - ታታሪው


18 views0 comments
bottom of page