top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የሰውን ላብ መብላት አይፈቀድም!!!(ደራሲና ጋዜጠኛ ጌቱ ሻንቆ)

Updated: Jun 9, 2019



የሰውን ላብ መብላት አይፈቀድም!!!

በሀገራችን ውስጥ ከስርቆት፣ መሰል ኢሞራላዊ ድርጊቶች ጋር ተያይዞ ፣ እንዲህ ያሉ ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች በተፈፀሙ ጊዜ ፣ ድርጊቶቹ ዳግም እንዳይፈጸሙ የሚያደርጉ ተግባሮች ይከናወናሉ።

በስውር የተፈፀሙ፣በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ነገሮችንም የማፈላለግና የማጋለጥ ተግባሮችም እንዲሁ ይከናወናሉ።

በደቡብ ኦሞዞን ከሚገኙት ብሄር ብሄረሰቦች መካከል፣ ከበና ብሄረሰብ አባቶች ከኛ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ቆይታችን የውይይት መልክ ያለው ነው። በመሆኑም ጠያቂና መላሽ አሉ።

የምላሾቹ ባለቤቶች ደግሞ አይቶሄ፣ አይታ ሁቼ፣ ሙጌ ጎኔ፣ ጌዳ ሀሬ የተባሉት የሀገር ሽማግሌዎች ናቸው፡-

1. በናንተ መካከል አንድ ሰው በስውር አንድ ወንጀል ፈፀመ እንበል። ይህን በስውር ወንጀል የፈፀመ ሰው እንዴት ነው የምትደርሱበት? አውጫጭኝ እንዴት ነው? ወንጀሉ የራስ ያልሆነን ነገር በስውር መውሰድ ቢሆን ።

ኦይታ ጎኔ ፡- አንድ ወንጀለኛ በስውር ወንጀል በፈፀመ ጊዜ። እኛ የሀገር ሽማግሌዎች ምንድነው የምናደርገው? ሽማግሌዎች ተሰብስበን፣ ያገሩንም ሰው አሰባስበን ማንነቱን የማጣራት ጥረት እናደርጋለን።

2. ማጣራት ሲባል እንዴት ነው? በስውር ነውኮ የተፈጸመው?

ኦይታ ጎኔ፡- ስርቆት የከብት ሊሆን ይችላል። ከብት በሚሰረቅበት ጊዜ፣ የሰረቀውን ሰው ለማወቅ ዱካውን ተከትለን ልንሄድ እንችላለን። ርቆ የሄደም ከሆነ። ከኛ አካባቢ ውጪ ወደሆነ ስፍራም የተጓዘ እንደሆነ። ዱካውን እየተከተልን እንሄዳለን፡፡ ዱካውን ተከትለን የደረስንበት። የደረስንበት የሌላ አካባቢ ሰዎችም ሁኔታውን ተረድተው እንዲተባበሩን እንጠይቃለን።

3. ዱካውን ያጠፋ፣ ዱካውን ተከትሎ መድረስ አስቸጋሪ ቢሆንስ? ምን ይደረጋል?

ኦይታ ጎኔ ፡- እንደዚህ ነው። ሰውየው የሄደበትን አቅጣጫ ለይቶ ለማወቅ የምንፈጽመው ባህላዊ ስርዓት አለን። ጫማ እንጥላለን። ጫማውን የሚጥሉ ባህላዊ አዋቂዎች አሉን። ጫማ የጣልን እንደሆነ ፣ሰውየው ተደብቆም አይደበቅም። ዱካውን አጥፍቶ አይጠፋም።

አይቴ ሁቼ ፡- በኛ ባህል ውስጥ እንዲህ ያለው ነገር ሲያጋጥም የሚሰሩ ደንቦች አሉ። እንደተባለው ነው። ለምሳሌ ጭለማን ተገን አድርጎ፣ ከብቶች ዘርፎ ሊሄድ ይችላል። ነገር ግን ግለሰቡን አላየህም። ጫማውን መጣል ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ሽማግሌዎች በሙሉ ተሰባስበው። አንድ ዛፍ ጥላ ስር ይቀመጣሉ። ሽማግሌዎቹ፣ “ አንተ ጨለማን ተገን በማድረግ ዘርፈኸን ሄደሃልና። በጨለማ የሰራኸውን በቀን ያጋልጥህ! ”፣ ብለው ይረግሙታል። የተረገመው ሰው፣ ከአካባቢው አብዶ ራሱን ሊያጋልጥ ይችላል። ወይም ደግሞ በድንገተኛ በሽታ ተይዞ መጨረሻው ሞት ሊሆን ይችላል።

ጌዳ ሀሬ፡- እንደዚህ ነው። እንደ አርብቶ አደር፣ እንደኛ አካባቢ ባህል። ማንኛውም ሰው የሰውን ላብ መብላት አይፈቀድለትም። የኔ የሆነ ከብት ሜዳ ላይ ሞቶ ቢገኝ። አንዳንድ ጊዜ ከብት ወይም ፍየል ዝም በሎ ሊሞት ይችላል። ማንም ጉዳት ሳያደርስበት። በምን አይነት በሽታ እንደሞተም ላይታወቅ ይችላል። ከብቱ ወይም ፍየሉ ምንም አይነት በሽታ ሳያገኘው፣ በሰው ዕጅ ሊሆን ይችላል ሞቶ የተገኘው። ሰውም ይሆናል የገደለው።

ሰው ከሆነ የገደለው እንስሳው ላይ የምንሰራው ባህላዊ ደንብ አለ። ከብቲቱ ሞታለች። ነገር ግን ማን እንደገደላት አላወቅኩም። ባይታወቅም ግን የሀገር ሽማግሌ ተሰብስቦ የገደላትን እና ገሏት የተደበቀውን ሰው ይረግማሉ። እርግማኑ እንደተደበቀ በዚያው አያስቀረውም። እርግማኑ ጫማ ተጥሎ ነው፣ እንስሳዋ በሞተችበት ስፍራ የሚፈፀመው።

ደንቡ ሲሰራ የሚፈፀም ሌላም ስርዓት አለ። የሞተችዋን እንስሳ አፍ እንከፍታለን። አፏን ከፍተን የግራር እሾክ አፏ ውስጥ እናደርጋለን። አፏ ውስጥ ካደረግን በኋላ ፣ “ሰው የገደለሽ ከሆነ፣ የገደለሽ ሰው እንደተደበቀ አይኑር። ይውጣ!” ብለን እንለምናለን፡፡ ይህ ልመናችን ሰውየውን አሩጦ ወደኛ ያመጣዋል።

በሰው እጅ እንስሳዋ ስለመገደሏና ስላለመገደሏ የምናጣራበት ሌላም እምነት አለን። እኛ ሰማይ ላይ የምትዞር ፣ የሞተን ከብት የምትበላ አሞራ አለች። ይህች አሞራ በሰው ልጅ የተገደለን ከበት ስጋ ወርዳ አትበላም ብለን እናምናለን። በዚህም ጉዳይ ሰው መሆኑን እንለያለን። የኛ እምነት ነው ይሄ። ዝምብላ የሞተች ከሆነ ግን የትኛውም አውሬ ወስዶ ይበላታል።

ከብቲቱ በስውር ተሰርቃ የተወሰደች እንደሆነ። ሌላም የሚፈጸም ባህላዊ ደንብ አለን። ʻካርኮʼ የምትባል የዕጽዋት አይነት ባካባቢያችን አለች። እሷን ይዘን እንደዚህ እናደርጋለን። (ከርኮን በእጃቸው እንደያዙ አይነት፣ እጃቸውን ከፍ አርገው እንደፒንዱለም ግራና ቀኝ አወዛወዙ)

4. እንዴት ማለት? ምን እያላችሁ?

ጌዳ ሀሬ፡- ምን ብለን ነው መሰለህ የምናደርገው? “ ፍየሌ፣ ወደኔ ነይ! በፊቴ ተገለጪ!”እንላለን። እምነታችን ነው። ይህን አድርገን ስንፈልጋት እናገኛታለን። ፍለጋ ባልሄድም በራሷ ጊዜ ወደኔ ትመጣለች። ይህም እምነታችን ነው። እቤቴ፣ በረቴ ድረስ ትመጣለች። እምነታችን ነው።

ሌላው ለምሳሌ፡፡ ያንተን ገንዘብ አንድ ሰው ዘርፉ ተሰወረ። ዱካው ግን አለ። ዱካውን እየተከተልክ ሄደህ። ዱካው በመሀል ቢጠፋብህ። ወደኋላ ተመልሰህ ካየኸው ዱካው ላይ አፈር ትዘግናለህ።

“እኔ አንተን ምንም አልበደልኩህም። ሳልበድልህ የኔን ሀብት ዘርፈህ ሄደሃልና። ያንተ ያልሆነውን ሀብት ብላ!” ብዬ እናገራለሁ። እኔ ይህንን ብልም እርሱን ግን አይበላውም። አይምሮው ተነክቶ ይመጣል።

5. አንዳንድ ጊዜ፣ ህፃናት ያልተገባ ነገር ሊፈጽሙ ይችላሉ። ምን ታደርጋላችሁ?

ጌዳ ሀሬ፡- እንደዚህ ነው። አንድ ጥፋት በአካባቢያችን ተፈጽሞ ተገኝ እንበል። ጥፋቱ ተፈጽሞ እንደተገኘ። የአካባቢው ሽማግሌዎች ይሰበሰባሉ። ጥፋቱ በህፃናት የተፈፀመ ከሆነ፣ “ ይህ የልጆች ነገር ነው” ብለው፣ መርቀዋቸው ይነሳሉ። ልጆቹ ግን ዳግመኛ ጥፋት እንዳይፈጽሙ ይመከራሉ።

አሁንም እንደገና። ህፃናቱ ተጋጭተው እርስ በርስ የተፈነካከቱ ሊሆኑ ይችላሉ። በኛ ባህል ደም ማፍሰስ ነውር ነው። ደም ፈሶ መሬት ከነካ። ደም ማፍስሱ ነውር ነው ይባልና። ከማሽላ እህል ቦርዴ ይጠመቃል። እንጉዳይ ተፈልጎ እኩል ሁለት ቦታ ይሰነጠቃል። “ ከርኮ” የምትባለው እፅዋትም ተፈልጋ እኩል ሁለት ቦታ ትሰነጠቃለች።

ቦርዴው የተሰነጠቀው እንጉዳይና ኮርኮ ቀርበው። በመካከላችን የደም ጉዳይ የለም ተብሎ ስርየት ይደረጋል። እንደዚህ ነው የኛ ባህል።

ሙጌ ጎኔ፡- ፍየሎች፡፡ በረት ሙሉ ፍየሎች ሊጠፋ ይችላሉ። ተሰርቀውም። በመንገድ አሳችነትም ቢሆን ይችላል የጠፉት። እንዲህ ያለው ነገር ሲያጋጥም። ሌላም የምንፈጽመው ስርዓት አለ። ህፃን ልጅ ይመረጣል። የተመረጠው ህፃን ልጅ በረቱን ይዞራል። ከዞረ በኋላ “ የጠፋችሁትን ፍየሎች፣ እናንተን ፈጣሪ በሰላም ይጠብቃችሁ! ጠብቆ ያምጣችሁ!” ብሎ ፀሎት ያደርሳል።

6. ፈጣሪ በናንተ ቋንቋ ምን ተብሎ ነው የሚጠራው?

ሙጌ ጉኔ፡- ዋኮ

7. የዋኮ መኖሪያ የት ነው?

ሙጌ ጉኔ፡- ሰማይ ላይ አለ ብለን ነው የምናምነው። ደንቡን ስንፈጽም ፍየሎቻችን ምንም ጉዳት አይደርስባቸውም ብለን እናምናለን።

8. ስለጠፋት ፍየሎች ሰላም ፀሎት እንዲያርስ ህፃን ልጅ መመረጡ በምን ምክንያት ነው?

ሙጌ ጉኔ ፡- ሀፃን ልጅ የተመረጠበት ምክንያት። አዋቂ የሆነ ሰው የተለያዩ ሀጢያቶችን ሲፈጽም ይገኛል ብለን ስለምናምን ነው። ህፃኑ ግን ከምንም እርኩስ ድርጊቶች ንፁህ በመሆኑ ምክንያት ነው። በርሱ ንጽህና ምክንያት ወደኛ የጠፉብን ጠፍተው እንዳይቀሩ ለመጠየቅ ነው።

ፍየሎች ማታ ጠፍተው ሊሆን ይችላል። ጠዋት ተነስቼ ሽንት ሳልወጣ፣ ከርኮ ይዤ ወደኔ ይቀርቡ ዘንድ እጠይቃለሁ።

9. እኔ አጠፋሁ ልበል። በሰውር ነው ጥፋቴን የፈጸምኩት። እናንተ ደግሞ በስውር የተሰራው በገሀድ ይገለጥ ዘንድ ደንቦቻችሁን ስራችሁ። የስራችኋቸው ደንቦች ወደናንተ አንቀዥቅዠው አመጡኝ። መጨረሻዬ ምንድነው?

ጌዳ ሀሬ፡- ተንቀዥቅዦ ከመጣ። እንደዚህ ነው የምናደርገው። መጀመሪያ እኛ በርሱ ላይ ደንብ ሰርተን አይደል። የሰራነው ደንብ አንቀዥቅዠው። ተንቀዥቅዦ ወደኛ መጣ።

ተንቀዥቅዦ ወደኛ ከመጣ በኋላ ። ቤተሰብቾ አሉት። አባት ሊኖረው ይችላል። ወንድም ሊኖረው ይችላል። ሚስትም ልትኖረው ትችላለች። ቦርዴ ይዘጋጃል። ቡና ይፈላል። የሀገር ሽማግሌዎች በተዘጋጀው ቦርዴ እና ቡና ዙሪያ ተሰባስበው።

በካርኮ አይደለም የተረገመው። ካርኮም ትቀርባለች። ካርኮዋ ቦርዴ ውስጥ ትነከራለች፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ይህ ሰው እንደዚች ካርኮ መልካም መዓዛ ይኑረው። ሽታው የሚያውድ ይሁን ተብሎ ይመረቃል። ቦርዴውም ይጠጣል። ቡናውም ይጠጣል። ሰውየውም ከሰዎች ጋር ይቀላቀላል። ይህ ስርዓት ከተፈፀመ በኋላም ወደ ቀድሞ ጤንነቱ ይመለሳል ብለን እናምናለን። ስርየት ተደርጎለታል። ይኸው ነው።

10 - አመሰግናለሁ፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛ ጌቱ ሻንቆ


16 views0 comments
bottom of page