1. ዋርዳው መጣና ቆይ አለኝ አንድ ዓመት
ጫትክን እየበላህ ሳታድር ከሴት
አምሬን እየሞላህ ጠጅን ሳታሸት
ደረሳህን ይዘህ ሳትወጣ ከቤት
እኔም ኸልዋ ገባሁ ቆየሁ አንድ ዓመት::
2. አንድ ዓመት ጫት ቅመን ዓለሙን ስንድር
ንጉሥ እየፈራኝ ሳይጠላኝ አሽከር
ወዲያው ስሜ ታውቆ ሸዋና ሐረር
እኔም በመስታወት ዓይኔን ሳሳምር
ቃሌ ሳይዛነፍ ሳልደናገር::
3. አላህ ሲያሳምረው ሰው እጣው ሲወጣ
ዓመት አስቀመጠኝ ከኸለዋ ሳልወጣ
ወዲያው መናም አየሁ አንበሳ ሲወጣ
ነብር እየመራኝ ጅብ ከፊቴ መጣ
ግመል ተሸክሞኝ የሆነ መላጣ::
4. መናቡ አይቼ ለሰው ሳላወራ
በሰባተኛው ቀን መጣ አንድ ቀብራራ
መሰንቆና ዋሽንት በእጁ ይዞ ጭራ
ከኔ ጋራ አደረ ጫት ሲቅም ሲያወራ
መሰንቆ እየመታ ሲዘፍን ሲያቅራራ::
5. አላህ ሲያሳድገው ነገሩ ሲሰላ
በስምንተኛው ቀን ጫት ስንቅም ስንበላ
ድቤ ተሸክሞ መጣ አንድ ሻንቅላ
ጫት በጨርቅ ይዞ ጠጅ በሸክላ
ሁሴን ቡን አፍላልኝ ነገሩ እንዲሰላ::
6. ስምንት ቀን ከደምኩ ሳትናገር አፌ
የቤቴን ግድግዳ ግንዱን ተደግፌ
ፊቴን እያጠብኩኝ እንዳይመጣ እንቅልፌ
እንዲቀመጡበት ጋቢዬን አንጥፌ
አይገርማችሁም ወይ ሳልነግድ ማትረፌ::
ጌቴ ገላዬ (ዶ/ር)