top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ስንፍናን የምንቀርፍባቸው 10 መንገዶችስንፍናን የምንቀርፍባቸው 10 መንገዶች

ስንፍና ምንድ ነው? ስንፍና ጥረት እንዳናደርግ እና ጠንክረን እንዳንሰራ የሚያደርግ የውስጥ ግፊት ነው። ይህም ብዙ ጊዜ ነገሮች ባሉበት እንዲቀጥል የሚያደርግ ሲሆን አንዳንዴ ትንሽ ሰነፍ መሆን ያስደስተናል። ለምሳሌ ከረጅም አድካሚ የስራ ሰዓት ቡኋላ ወይም በጣም ቀዝቃዛማና ሞቃታማ በሆነ ቀን። ሆኖም ይህ አይነቱ ሁኔታ ቀጣይነት ካለው የሆነ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል።

ስራችነን በብቃት ለመስራት ንቁና ስኬታማ ህይወት ለመምራት ስንፍናን እንዴት መቅረፍ እንደምንችል መማር ይኖርብናል።

1. አንድ ግዙፍ አድካሚ መስሎ የሚታየንን ስራ ወደ ትንንሽ ስራዎች እንቀይር

ብዙ ጊዜ ስራዎቻችን በጣም ግዙፍ ፣ አድካሚ ፣ አሰልች ወይም ብዙ ጊዜያችነን የሚሻሙብን ሁነው ስለምናገኛቸው እነዚህን ስራዎች እናስወግዳለን። ታዲያ አንድ ስራ ወደትንንሽ ስራዎች መከፋፈላችን ይህን ችግር ሊቀርፍ ይችላል። ይህን ማድረግ ከቻልን ስራችነን አድካሚና አስቸጋሪ መስሎ አይታየንም፤ ብዙ ጥረት ማድረግም አይጠይቀንም።

ለምሳሌ:- አንድ ሰው በጣም ወፍራም ቢሆንና ውፍረቱ ለጤናው አስጊ በመሆኑ 9ኪሎ እንዲቀንስ ቢነገረው ይህ ሰው 9ኪሎ በአንድ ቀን ሌሊት ቀንሶ ማደር አይችልም። እንዲሁም በ1 ወር ውስጥ 9 ኪሎ መቀነስ ከባድ ነው፤ አይደለም እንዴ? ስለዚህ ይህ ሰው ስራው አድካሚና አሰልች እንዳይሆንበት በአንድ ወር ሶስት ኪሎ ቢቀንስ በ3 ወር ውስጥ የሚፈልገው ደረጃ ላይ ይደርሳል ማለት ነው።

2. የእርፍት እና የእንቅልፍ ጊዜ ይኑረን

አንዳንዴ ስንፍና ከመጫጫን ስሜትና ሃይል ከማጣት ጋር የተያያዘ ነው። ታዲያ እንዲህ አይነቱን ስንፍና ለመቅረፍ የዕረፍት እና በቂ የእንቅልፍ ጊዜ ሊኖረን ብሎም ለሰውነታችን ንፁህ አየር ልንሰጠው ይገባል። እንቅልፍ የተረጋጋና ንፁህ እምሮ እንዲኖረን የሚያደርግ ሲሆን ሙሉ አካላችን እንዲያርፍና እራሳችነንም ለተሻ ስራ እንድናነሳሳ ያግዘናል። ከዚህ በተጨማሪ የአካል እንቅስቃሴ ብናደርግ ሰውነታችን ይፍታታል።

3. ተነሳሽነት

ሌላኛው የስንፍና ምክኒያት ተነሳሽነት ማጣት ነው። ስለ ስራሳችን መልካምነት ፣ ስራችነን የማከናወናችን ጠቀሜታ ፣ የግባችንን ብሩህ ተስፋ በማሰብ ተነሳሽነታችነን ማበርታት እንችላለን።

4. ምን እና ማንን መሆን እንደምንፈልግ ራዕይ ይኑረን

ዘወትር መሆን የመንፈልገው አይነት ሰው ለመሆን ማሳካት በምንፈልገው አላማ እና መኖር በምንሻው ህይወት ዘወትር ማንፀባረቃችን እና ለሱ መልፋታችን ስራ እንድንሰራ ተነሳሽነትን ይፈጥርልናል።

5. ስልጥቅሞቹ እናስብ

ስለ ችግሮች ወይም ስለ መሰናክሎች ከማሰብ ይልቅ ስንፍናን በመግራታችን የምናገኘውን ጥቅም ምን እንደሆነ አናስብ። ይህን ብናደርግ ምን ይፈጠራል(ምን ይገጥመናል) ብለን ስለችግሮች ወይም ስለ መሰናክሎች ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ ተስፋ እንድንቆርጥ፤ ስራ እንዳንሰራ እና ከአላማችን እንድንርቅ ያደርጋል።

6. የሚያስከትለውን ውጤት እናስብ

ለስንፍናችን ተሸንፈን ስራዎችን የማንሰራ ከሆነ ምን ሊያስከትል እንደሚችል እናስብ። ስንፍና ምን ጊዜም ጥገኛ ሁነን እንድንኖር የሚያደርግ ራስ ወዳድ የውስጥ በሽታ ነው። ታዲያ በሌሎች ላይ ጥገኛ መሆን ለቤተሰብም ሆነ ለሐገር ትልቅ ትልቅ ሸህም ይፈጥራል። ይባስ ብሎ ትልልቅ ወንጀሎች ላይ እንድንወድቅ በር ይከፍታል።

7. በተወሰነ ጊዜ ውስጥ አንድን ስራ ብቻ እንስራ

ሁለት ወይም ሶስት ስራ በተመሳሳይ ሰዓት የምናከናውን ከሆነ የድካም ስሜት እንዲሰማን በማድረግ ወደ ስንፍና ይመራናል። ለምሳሌ አንድ ተማሪ በጥናት ጊዜው ለፈተና እያጠና ቢሆን በአንድ በበኩል ደግሞ የቤት ስራውን ይሰራል። በአንድ በኩል አዳዲስ ቃላትን ይሸመድዳል። አስብት በተመሳሳይ ሰዓት ማለት ነው። ታዲያ ይህ ተማሪ ትኩረቱ ምን ላይ ነው? ከጊዜ ቡኋላ የማስታወስ እድሉ ምን ያህል ሊሆን ይችላል?

8. ስራዎቻችነን እንደ እንቅስቃሴ እናስባቸው

እያንዳንዱን ስራ እንደሚያጠነክሩን፤ ወሳኝ እና ታታሪ እንደሚያደርጉን የአካል እንቅስቃሴዎች እናስባቸው።

9. ነገዛሬ ማለት(ማዘግየት)

እንደኔ እንደኔ በሰዎች ልብ ነግሶ የሚገኝ ትልቅ በሽታ ቢኖር ነገዛሬ ማለት ነው። ይህ አንዱ የስንፍና ክፍል ሲሆን ብዙ ጊዜ ነገ እንሰራዋለን በማለት ስራዎቻችነን ነገ ነገ እያልን ለረጅም ጊዜ ሳንሰራ እናቆያለን፤ ስራውን ሳንሰራ መስራት ያለብን ጊዜ አልፎ ቁጭ ይላል። የሆነ ነገር ማድረግ ካለብን ለምን አሁን አናደርገውም ወይም አሁን ማድረግ አለብኝ የሚል ቆራጥ ውሳኔ እንወስን። ዛሬ የምንሰራበት ሰዓት እያለን የሩቅን መመኘት ምን የሚሉት ሞኝነት ነው!!!

10. ከስኬታማ ሰዎች እንማር

ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ስንፍናን እንዴት እንደሚያሸንፉ እንመልከት፤ ከእነሱም እንማር። የስንፍናን ልማድ መቅረፍ የሚቻለው የዕለት ተዕለት ስራችነን ቀላል በሆነ መንገድ ስንሰራ ነው። ለዚህ ደግሞ ቁልፉ ስራዎቻችነን በእቅድ ለመስራት ስንጣጣር እና የታታሪነት ፣ የትጉህነት እንዲሁም የስራ ወዳድነትን ባህሪ ስንላበስ ነው!!!

ምንጭ - አህመድ የሱፍ (Youth-Mission የወጣቱ ተልእኮ)


122 views0 comments
bottom of page