top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

እኛና ኢትዮጵያችን (በሰሙ ቢንት ሽፋ)

Updated: Jun 9, 2019እኛና ኢትዮጵያችን

ኢትዮጵያን ሊገነቧት የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ ሊያፈርሷትም የሚሹ ጥቂቶች አይደሉም። ታዲያ ሁሉም ከባእድ ሀገር የመጡ ሳይሆኑ የአብራኳ ክፋይ የሆኑ የገዛ ልጆቿ ናቸው ። ኢትዮጵያን ማን ይገነባታል እንዴትስ የሚያፈርሳት ይኖራል? የሚል ጥያቄ አይጠፋም ። አዎ ኢትዮጵያን ሊገነቧት ብዙዎቹ ይፈልጋሉ ። አድጋ ፣ ተለውጣ፣ ከድህነት ተላቃ ፣ ዜጎቿ ከስደት ተላቀውና የህዝቧ አንድነት ሲያንፀባርቅ ማየት የሚፈልጉ በጣም ብዙዎች ናቸው ። ግን እነማን እንደሆኑ በእውን አይታወቅም። ምክንያቱም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ ከአንገት በላይም ይሁን ከልባቸው ባይታወቅም ኢትዮጵያ ስትነካና ስታዝን ህመሟ ህመሜ ነው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም ። በኢትዮጵያዊነቴ አልደራደርም ኢትዮጵያዊነቴ ኩራቴ ነው የሚሉም በጣም ብዙ ናቸው ።

በእውነቱ አዎን ኢትዮጵያዊነት እኮ ኩራት ነው ። ግን ላወቀው ብቻ ነው የሚሆነው ። ሀገርን በእናት ምትክ የምንጠራም ጥቂቶች አይደለንም።

ግን እነማነን…?

ህዝቡ…?

መንግሥት…?

ወይስ ተማሪው… ? አይታወቅም !

በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያን ሊያፈርሷት የሚፈልጉ ጥቂቶች አይደሉም ። እነሱም እነማን እንደሆኑ በርግጥ አይታወቅም ። ምክንያቱም ከላይ እንደገለፅኩት ሁሉም ለኢትዮጵያ ሀገሬ ነው የምሰራው የሚል ሀሳብ ሲያመነጭ ይደመጣል ።

አሁን ባለንበት ሁኔታ ወይም በምናየውና በምንታዘበው ሀገራዊ ሁኔታ ግርምትን ይፈጥራል ። ምንድነው ደግሞ ግርምት የሚፈጥረው የሚል ሀሳብ ይነሳ ይሆናል ።

አዎን… እሱም ከክልል ይገባኛል አንስቶ እስከ ቀበሌ የይገባኛል ወይም ይህ መሬት የኔ ነው እና መሬቱ በታሪክ የኔ ነበር የሚለው የሀገራችን ህዝብ ሲታይ ግርምት ይፈጥራል ።ያሳዝናልም።

ይህ የይገባኛል ጥያቄ ኢትዮጵያ ሀገራችን እየገነባት ነው ወይስ እያፈረሳት ?

ግን አንድን ነገር ረስተናል፡- መሬት የፈጣሪ መሆኑን እና እኛ ከመሬት (ከአፈር) ተፈጥረን ወደ መሬት እንደምንመለስ ዛሬ ግን የኔ ነው በሚል የእርሱ… የመሬቱ መሆናችን ረስተናል ። እንደ ሀገራዊ ደግሞ ስናስብ ለዚች ሀገር የለፉላት አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን የከፈሉት መሰዋእትነት ደማቸው ደመ ከልብ እንዲሁም አጥንታቸው እንኳ ስርአተ ቀብር ሳይፈፀምላቸው ኢትዮጵያ የሚባል ሀገር እንዳትጠፋ ከሚወዱት ቤተሰቦቻቸው ተለይተው ሀገራቸው አስቀድመዋል ።

አዎ… እውነትም የኢትዮጵያ ፍቅር የነበረባቸው አልፈዋል ። ዛሬም ላይ በጥቂቱ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ብለው በየድንበሩና በየጉራንጉሩ በረደኝና ሞቀኝ የማይሉበት እንዲሁም ቤተሰቤ ናፈቀኝ ወይመ ቤተሰብ ልመስርት በማይሉበት ሁኔታ ውስጥ ሀገራቸውና ህዝባቸውን ለመጠበቅ ለአመታት ውጪን ብቻ የሚያድሩ ጥቂቶች አይደሉም ። ቤት ይቁጠረው ነው እንጂ !

በተቃራኒው ደግሞ በምን ቸገረኝ የምንጓዝና ለኢትዮጵያዊነታችን ግድ የማይሰጠን ሺ አመት አልኖርባት የሚል አመለካከት የያዝንም ጥቂቶቹ አይደለንም ።

ግና እንደዚ ለማሰብና ማንኛውም ነገር ለማድረግ ምን አነሳሳን ?? እኛ እኮ ኢትዮጵያዊ ነን ። ኩሩ ታሪክ ያለን በብዙዎች ዘንድ የሚቀናብን ። ደግሞም… ለምን ይቀናብናል የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል ።

አዎ… ይቀናብናል !

ምክንያቱም የሀይማኖት እኩልነትና መከባበር አለን ከዚህ በፊት በብሄርና በይገባኛል ጥያቄ ተፈራርቀን አናውቅም ። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ባወረሱን አንድነታችን ልዩ ማንነታችን ነበር ። ይህ መለያችንና የሚቀናበቱ ተግባራችን ነበር ።

ዛሬ ላይ ግን እርስ በእርሳችን አንተ የዚህ ብሄር ነህ አንተ የገሌ ዘር ነህ የሚል መሪ ቃል ይዘን እርስ በእርስ እየተባላን ፣ እየተገዳደልን፣ እያፈናቀልን፣ አንዱ ተሰዳጅ አንዱ አሳዳጅ ፣ አንዱ አሸናፊ ከፊሉ ለሀገርና ለህዝብ ሰላም ሲል ተሸናፊ ገዳይና አስገዳይ፣ ገፊና ተገፊ፣ ሆነናል። ከባእድ ሀገር የመጣ ዜጋ እንጂ ትውልደ ኢትዮጵያ የማንመስል ትላንት አያቶቻችን ያወረሱንን አንድነት ረስተን ጠላቶች ሆንን ። ይህ ሁሉ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ስንፈፅም እውን ፈጣሪ እንፈራለን ? ፈጣሪውን የሚፈራም ይኖራል ። ሌላው የሀገሪቱን የህግ የበላይነት በስንቶቻችን ይከበራል ? ለህግ ተወክለው የሚሰሩት እውነት ለህሊናቸው ይሰራሉ ? ወይስ በተለያዩ ቀረጦች የተጠራቀመው የህዝብ ገንዘብ ወደ ባለስልጣናት እጅ ሄዶ ለብሄር እገዛ ወይም ለሙስና አገልግሎት እየዋለ ነው ? ያ… ማለት ታማኝ የሆነና ለህሊናው ያደረ በተጨማሪም በሚሰጠው ደሞዝ ብቻ የሚሰራ የመንግስት ሰራተኛ አለ ለማለት ይከብዳል። ምክንያቱም እውነተኛና ለህሊናቸው ለህዝብ የቆሙ ስራ ወዳዶች በዚህ በአለንበት ዘመን በባለስልጣናት አይወደዱም ። አልፎም ያለወንጀላቸው ከርቸሌ መወርወር ይሆናል እድላቸው ።

ግና… እውሸት የቱንም ያህል ብትሮጥ እውነትን መቅደም አይቻላትም ። እውነትም ምንም ያህል ብትሟሟ እንኳን አትጠፋም። እውነት አንድ ናት ። ውሸት ለሀገር አፍራሾች እና ለሆድ አደሮች በጣም ቅርብ ጓደኛ ናት ።

ብቻ ከምንም በላይ ለኢትዮጵያችን ስንል እኔ ማነኝ? እንበል ! በርግጥ ሆዳሞች ይፈርሳሉ እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም ።

ኢትዮጵያ ለእኛ ታስፈልገናለች!

እኛም ለኢትዮጵያችን እናስፈልጋታለን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ተጻፈ - በሰሙ ቢንት ሽፋ (Semu Bint Shifa)


33 views0 comments
bottom of page