የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች (ክፍል - 07)

37. ድርቡሽ ጥሩ እስላም ልባቸው የጠራ
ሶላትን አይተውም ቢበዛበት ሥራ
ችግርም ቢገጥመው ይችላል መከራ
አገራቸው ሜዳ የለውም ተራራ
ልብሳቸው ቀሚስ ነው የለውም ዳኢም ታጥቀው ሥራ::
38. ከእኔ ተመርቀው ሴት ልጅ ከወለዱ
ለጉግሳ ይዳሯት እንዳትዛመዱ
ሌላም አያገባት ፈርዶታል ዘመዱ
እንግዲህ እሜቴ ጫት ቃሚን ይውደዱ
አሁን ነው መሸመት ደጎቹ ሳይሄዱ::
39. በአዳራሹ ገብተህ በእልፍኙ ላይ ውጣ
በእልፍኙ ላይ ገብተህ በአዳራሹ ውጣ
እንደምንም ብለህ ሸዋረጋን አምጣ
የተያዝክ እንደሆን እኔ በጉድ ልውጣ
እኔ ፈርጃለሁ ሌላ እንዳታመጣ::
ወንድ ትወልዳለች ግን የለውም ዕጣ::
40. በራስህ ገብቼ በሆድህ ብወጣ
ከትርንጎ በቀር ሌላ ምንም ታጣ
ይኸ ያልሆነ እንደሁ እኔ በጉድ ልውጣ
ሆድህን የሚገልጥ ሽማግሌ ይምጣ
ይኸንን ጉድ ሳላይ ከቤትም አልወጣ::
41. ተው አቶ ሙቀጫ እኔን አታላግጣ
ጌሾና ቡናህን ውጣና ቀጥቅጣ፣
በሽታም እንደሆንክ እኔ በጉድ ልውጣ
ማንን ታሞኛለህ እኔ አልወድም ላግጣ
እኔ እሳት አልገባም ነግረንሃል ቁርጣ::
42. ምኒልክ ክፉ ነው በስንቱ ፈተነኝ
እንድአለፉት ጠንቋይ በእሳት ሊያቃጥለኝ
በሰው እጅ አልጠፋም አላህ ካልገደለኝ
እንኳን ከመምሬ ፊት አላህ ሊቅ አረገኝ
እፈራው ነበረ በጅኑ እንዳይጠልፈኝ::
43. የምኒልክ ጠንቋይ ዋና ደብተራው
ያስፈጨው ነበረ ጅኑን እንደ ሰው
በርበሬ ነበረ የሚቋደሰው
ጅኑን እየላከ ስንቱን ሰው ፈጀው
መምሬ ሐሲድ ነው ከመጀመሪያው::
44. እንግዲህ ወንድሜ ስማኝ የኔን ፍርድ
መውለድህ አይቀርም ከጭን ከገረድ
ቁርኣን የሚቀራ ኢልምን የሚወድ
መጨረሻው ከፍሮ ካልሆነ ፈሳድ::