top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

አቧራውን ማስጨስ ስታቆም መንገዱ በግልጽ ይታይሃል! (በሚስጥረ አደራው)

Updated: Jun 9, 2019አቧራውን ማስጨስ ስታቆም መንገዱ በግልጽ ይታይሃል!

እንደ ሳይንሳዊው መረጃ ከሆነ የሰው ልጅ ከ50,000-80,000 ሃሳቦች በቀን በአይምሮዋችን ይመላለሳሉ። ከዚህ ሁሉ ሃሳቦች ውስጥ አብዛኛዎቹ በቀን በቀን የምንደጋግማቸው ተመሳሳይ ሃሳቦች ናቸው። ለዚህም ነው ህይወታችን የአስተሳሰባችን ነጸብርቅ የሚሆነው። በእውን ሆኖ የምናየው ነገር ሁሉ በመጀመሪያ በአይምሮው ውስጥ የተቀነባበረ ነው። በራሳችን ህይወት ላይም ሆነ በመላው አለም ላይ የተከወኑ ነገሮች ሁሉ መጀመሪያ ሃሳቦች ነበሩ።

ከ50,000 በላይ ሃሳቦች አይምሮዋችንን ውስጥ ይመላለሳሉ ካልን፤ ምን ያህሉ ይሆን የሚጠቅሙን? እራሳችንን የመቀየር ሀሳብ ካለን ቅድሚያ አስተሳሰባችን ምን እንደሚመስል መቃኘት አለብን። ረጋ ብለን ለደቂቃ በጥሞና ውስጣችንን ብንሰማ፤ እጅግ እንገረማለን። ሃሳባችን አንዴ ከትላንት፤ አንዴ ከዛሬ አንዴ ከነገ፤ ሳያቋርጥ ይጋልባል። ልክ ያለማቋረጥ እንደሚማሰል ኩሬ መንፈሳችንን ያደፈርሰዋል ። ለዚህ ነው የምንፈልገውን ነገር ማግኘቱ የሚከብደን፤ የምንመኘውን ኑሮ መኖር ያቃተን፤ መረጋጋት የተሳነን፤ አይምሮዋችን አለማቋረጥ የማይጠቅሙንን ሃሳቦችን ስለሚያመነጭ ነው። ላዎ ትዙ “ለተረጋጋ አይምሮ አለም ትገዛለታለች” ያለው፤ አይምሮዋችን እረጋ ሲል እና በዛሬ ላይ ትኩረታችንን ስናደርግ፤ ነገሮች ያለብዙ ልፋት እና ጭንቀት እውን ይሆኑልናል ማለቱ ነው። ጭንቀት እና መረበሽ መንስኤአቸው ዛሬ ላይ አለመኖር ነው። ትላንትን የሚያስብ ሰው እንዴት ዛሬን ማለፍ ይችላል? በአይምሮዋችን የምንሸከመው የትላንት ቅራቅንቦ እንዴት ዛሬን በረጋ መንፈስ ያሳየን? ያለጊዜው ስለነገ ስናስብ እና ስንጨነቅ፤ ዛሬን በደመነፍ እየኖርን ነው።

በሀሳብ የሚተራመስን አይምሮ ይዞ መኖር፤ በበረሃ ውስጥ ከነፋስ ጋር እንደመጓዝ ነው። ነፈሱ አሸዋውን እያንቦለቦለው መንገዳችንን ጥርት ባለ መልኩ እንዳንመለከተው ያደርገናል። ችግሮቻችን በህሊናችንን ውስጥ ከመጠን በላይ ሲመላለሱ፤ መፍትሄውን እንዳንመለከት አቧራውን እያስጨሱብን ነው። ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው? የሚከተሉት አራት ነጥቦች እረፍ ያጣን አይምሮ ለማረጋጋት ይረዳሉ

1ኛ- ከሁሉም በፊት የሚቀድመው ማስተዋል ነው። አይምሮዋችንን እንደታዛቢ መመልከት መጀመር አለብን። አሁን የማስበው ምንድን ነው? እያልን እራሳችንን መጠየቅ ስንጀምር፤ ሃሳባችን ያለቦታው ሲረግጥ እንይዘዋለን፤ ይህ ደግሞ ሃሳባችንን መቆጣጠር እና መስመር ማስያዝ እንድንችል ያደርገናል።

2ኛ- ለራሳችን ግልጽ መሆን መጀመር መቻል- እንደ ግልጽነት ህይወትን የሚያቀል ምንም ነገር የለም። ግልጽነት ሲባል ለሌሎች ሰዎች እውነትን መናገር ብቻም ሳይሆን እራስንም ጭምር ማወቅ ነው። ለራሳችን ግልጽ መሆን ስንችል የምናስባቸው ሀሳቦችን በጠራ መልኩ ማየት እንችላለን።

3ኛ- ነገሮችን ጨርሰን እንጀምር-በአብዛኛው ጊዜ አይምሮዋችን ትርምስምስ የሚለው፤ የምንፈልጋቸውን ነገሮች አስቀድመን እንዴት ማድረግ እንዳለብን ሳናውቅ ስንጀምራቸው ነው። ልክ የቤቱን ካርታ ሳይዝ ቤት መስራት እንደሚጀምር ነው።የምንሰራውን ቤት ሳናውቅ፤ ሲሚንቶ እና አሸዋችንን ብናላውስ ትርፉ ድካምና መረበሽ ይሆንብናል። በመኝታ ክፍሉ ቦታ ሳሎኑ፤ በሳሎኑ ፈንታ ሽንት ቤቱን እየጠፈጠፍን ለኛ የማይመች ቤት የምንገነባው በመጀመሪያ የቤታችን ካርታ ተነድፎ ስላለቀ ነው። ስለዚህ አስቀድምን የምንሄድበትን ማወቅ ከቻልን፤ እራሳችንን ከምዙ ጭንቀት ልናድነው እንችላለን።

4ኛ- በመጨረሻ በጭንቀት የምንለውጠው ነገር እንድሌለ እንወቅ፤ ለውጥ በጠንካራ ሃሳብ እና በተግባር እንጂ በጭንቀት እውን ሆኖ አያውቅም።

ሃሳባችንን እናቅልል፤ ዛሬን ለዛሬ፤ ነገን ለነገ እናውለው። አይምሮዋችን ሲረጋጋ እና የሃሳብ ኩሬያችንን ማማሰሉን ስናቆም፤ ጭቃው ወደታች መዝቀጡ አይቀርም። መንፈሳችን እረጋ ሲል ችግሮቻችን ለብቻ ወደታች ይዘቅጣሉ፤ መፍትሄዎቻችን ደግሞ ከላይ ይንሳፈፋሉ። ያኔ ሁሉም ነገር ግልጽ ይሆንልናል።ያለማቋረጥ የምናሰብ እና የምንጨነቅ ከሆነ ግን ችግሮቻችንን እና መፍትሄዎቻችንን እያማሰልናቸው ነው። የተረጋጋ አይምሮ ላለው ሰው አለም ትገበርለታለች የተባለውም ለዚህ ነው።

አይምሮዋችንን ካልተቆጣጠርነው ፤ እንዳሻው መጋለቡ አይቀርም። ከትላንት ዛሬ፤ ከዛሬ ነገ እየጋለበ መሄጃ እንዳያሳጣን እንጠንቀቅ። ትኩረታችንን ዛሬ ላይ አናድርግ፤ ሃሳቦታችት ሁሉ እናጢናቸው፤ የሚጠቅሙንን አናሳድጋቸው፤ የማይጠቅሙንን በጊዜ እናሰናብታቸው። በህሊናችን በር ላይ ዘብ መቆምንም መማር አለብን። ድፎ ዳቦ መድፋት የሚፈልግ ሰው፤ ወደ ማቡኪያው የዳቦ ዱቄት እንጂ ሽሮ አይከትም። የእኛም ኑሮ እንደዛው ነው፤ የምፈልገውን ውጤት ለማግኘት፤ ውጤቱን ሊሰጡን የሚችሉ አስተሳሰብ እና እውቀቶችን ወደ አይምሮዋችን እንከታለን እንጂ፤ ምኑንም ምኑንም ማግበስበስ የለብንም።

በሚስጥረ አደራው

23 views0 comments
bottom of page