top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ (በእሙ - ኢሳን)

Updated: Jun 9, 2019



ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ

ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ ሲባል ከቃሉ የምንረዳው የሰዎችን የእርስ በእርስ መረዳዳትን፣ መተባበርን ብሎም መደጋገፍን ለመግለጽ ጭምር ነው። ታዲያ ዛሬ ላይ ከራስ ወዳድነት ወጥተን አንዳችን ላንዳችን ስናደርገ የምናስተውለው መልካምነት በጣም የሳሳ ነው። ወንድማማችነቱ ወይም እራስን በራስ መተባበር እና ማገዙ ወይም አንዳችን በአንዳችን ውስጥ በመልካም ከሌለን ባዶ ነን። ወይም መዳረሻችን ከንቱ ነው የሚሆነው። ለምን ቢባል ፈጣሪ ሲፈጥረን በመልካምና ለመልካም ብቻ ነበር።

ብዙ ግዜ ከመልካምነታችን ወጥተን ሰውን ስንበድል እና ህሊናችን ሲወቅሰን ሰይጣን አሳስቶን ነው እንላለን። እኛ እራሳችን የመጥፎ ተግባሩ ባለቤት ሆነን በሰይጣን ማሳበብ ምን ይሉታል ? እንደ እኔ እምነት በእዚህ በተቀደሰው የረመዳን ወር ሰይጣን ታስሯል። ታዲያ ሰይጣኑ ከሌለ እኩይ ተግባሩን ማን ነው የሚወጥነው? ማንስ ነው የሚተገብረው ?

መልካም ንግግር ሰደቃ ነው ይባላል! እናም እጆቻችን መጥፎ ነገር ከመስራት እንዲሁም አንደበቶቻችን መጥፎን ነገር ከመናገር ተቆጥበው በወንድማማችነት ስሜት ፍጹም በሆነ ሰላም መዋደድ ስንጀምር እና ጓደኞቻችን ሲያገኙ ብሎም ሲለወጡ የእኔ ብለን መደሰት ስንጀምር ያኔ… እርስ በእርስ መገፋፋቱ እና መቀናናቱ አይኖርም።

ከመቀበል ይልቅ መስጠት ደስታን ይሰጣል። እናም መልካሙን መስራትና ያለንን ማካፈሉ በረመዳን ወር ብቻ የተፈቀደ ይመስል አስራ አንድ ወር መልካምኑን ነገር ሳንሰራ ለአንድ ወር ብቻ ብንሰራ ወይም ለአንድ ወር ብቻ ከወትሮው በተለየ ብንዋደድና ብንተዛዘን ለሰራነው መልካም ስራ የሚከፈለን ምንዳው በረመዳን ወር ብቻ ነው የሚሆነው? እንደ… እኔ እንደ… እኔ ከሆነ አስራ ሁለቱን ወር በሙሉ በስሌት ሳይሆን ንጹህ በሆነ መልካምነት ብንረዳዳ ሌላውን ከመጣል ይልቅ ብናነሳ! ሌላው የሰራውን ነገር ከማኮስመንና ከማንቋሸሽ ይልቅ ብናበረታታ መልካምነታችን እራሱ መልሶ መልካምን ይከፍለን ነበር።

ጎበዝ… የእራሳችንን እኩይ ተግባር በሰይጣን እያሳበብን ከምንኖር ወደንና ፈቀደን ለመልካምነት ብንዘጋጅ ከእጃችን ያለው ከእኛ ተርፎ ለብዙ እኛዎቹ ይበቃል። አባት ያልገነባውን ልጅ አይወርስምና ለልጆቻቻን ወይም ለችግኞቻችን መልካምነትን ብቻ እናውርስ።

እሙ - ኢሳን

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ


46 views0 comments
bottom of page