top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

መቆረጥ ያለበት ተስፋ (በሚስጥረ አደራው)

Updated: Jun 9, 2019መቆረጥ ያለበት ተስፋ

የጥበቃ ልኩ ምን ያህል ነው? በተስፋና በከንቱ ጥበቃ መካከል ያለው መስመር ምን ያህል ቀጭን ነው? በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተስፋ ቢኖርስ? አንዳንድ ነገሮች ላይመጡ ያስጠብቁናል፤ ተስፋ መቁረጥ አልያም መተው፤ ከተስፋ መቁረጥ በተለየ አወንታዊ የሚሆንበት አጋጣሚ የለም?

ጎረቤቴ ነው፤ ይህ ሰዓሊ። ሰዓሊ ያልኩት አዘውትሮ ቀለምና ብሩሹን ይዞ ገርበብ ካለው በራፉ ላይ ስለሚቀመጥ ነው። ተመሳሳይ የስዕል ሸራ ተመሳሳይ ቀለም ይዞ አየዋለሁ። ሁሌም ጸሃይዋ ስትፈነጥቅ በሩን ገርበብ አድርጎ በራፉ ላይ ካለች አንዲት በርጩማ ላይ ይቀመጣል። ሸራውን አርሶ መሳል ይጀምራል። በዚህ ተመሳሳይ ሂደት ብዙ ጊዜያቶች አለፉ፤ የማያልቅ ስዕል ሲስል፤ የማይዘጋ በር ገርብቦ፤ ቀናት ቀናትን እየወለዱ….ብዙ ምሽቶች መሹ ፤ብዙ ንጋቶች ነጉ።

እኔም ይህንን ሰዓሊ ጎረቤቴን አዘውትሮ ማየቱ የውዴታ ግዴታዬ ነበርና፤ በመስኮቴ አሻግሬ አየዋለው። ያሳዝነኛል…..ገርበብ ያለው በሩ፤ አቀማመጡ፤ የማያልቀው ስዕሉ የተደበቀ ታሪኩን ሳልሰማው ያስገርመኛል። ከተገረበበው በር ጀርባ እንዳይወጣ የተፈለገ ወይስ እንዲገባ የሚጠበቅ ሰው አለ? በርን ገርበብ ማድረግ ሰውን እንዳይወጣ ከማድረግ ወይም እንዲገባ ከመጠበቅ በቀር ምን ፍቺ አለው? በር የብዙ ነገሮች ተምሳሌት ነው፤ የበር መዘጋት እና መከፈት፤ከህይወት እድልና ጉድለት ጋር ተመሳስለው አንዳቸው የአንዳቸውን ስም እየተኩ ሲነገሩ ይሰማል። ምናልባት ይህ እውነታ ይሆን የዚህን የሰዓሊ በር ሌላ ትርጉም እንድሰጠው ያስገደደኝ? የበሩ ገርበብ ማለት ህይወቱ በተስፋና በተስፋ መቁረጥ ማህል የቆመች እንደሆነ እያሳበቀበት ይሆን?

ስዕሉስ? ሰዎች የስዕል ሸራና የምኞት ሸራ ይመሳሰላል ይላሉ። ሰዓሊ በጨርቅ ሸራ ላይ አለም ላይ ሊያይ የወደደውን ይስላል፤ አላሚ ደሞ በምኞት ሸራው ላይ በህይወቱ ውስጥ ያላየውን ግን ሊያይ የሚወደውን ይስላል። ታዲያ በርና የስዕል ሸራ የሚያመራምሩ ነገሮች አይደሉም? ዛሬም ጸሃይ ፈግግ እንዳለች በርጩማውን ይዞ ወጣ፤ በሩን ገርበብ አድርጎ ተቀመጠ፤ ሸራውን ዘረጋ። ፊቴን ለሰላምታ ከፍና ዝቅ አድርጌ አልፌው ሄድኩኝ። በህሊናዬ የዚህን ሰዓሊ ህይወት አወጣለው አወርዳለው፤ ከቤቱ ውስጥ ማን አለ? የሚሳለው ስዕል ምንድን ነው? ሁሉም ሰው ባለታሪክ በሆነባት አለም ውስጥ፤ ሁሉም ሰው የተለማመደውን ገጸባህሪ በሚጫወትባት ህይወት ውስጥ፤ የአንዳንዶች ታሪክ ይበልጥ ያጓጓል። ከዚህ በላይ የራሴን መላምት መስጠቱ ታከተኝና በበነጋታው ልጠይቀው ወሰንኩ።

ስትስቅ እስኪስቁላት የማትጠብቀው ጸሃይ፤ ሰዓቷን ጠብቃ ፈገግ አለች። በመስኮቴ አሻግሬ የጎረቤቴን በር መክፈት እጠባበቃለው፤ አንዳንዴ ነገርን ሲጠብቁት በሰዓቱ ቢመጣም እንኳን የዘገየ ይመስላል። እኔም የሰዓሊው መውጫ ሰዓት የዘገየ መሰለኝ። ጠበቅኩኝ…..ደቂቃቃዎች…..ሰዓታት …..አለፉ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዓሊው በሩን ሳይከፍት ዋለ። እጅግ ስላሳሰበኝ፤ ከሰላምታ በቀር አውርቼው የማላውቀውን ጎረቤቴን፤ ሰላም መሆኑን ለማየት ወደቤቱ ሄድኩኝ። ለወትሮ ገርበብ ብሎ የሚውለው በር ጥርቅም ተደርጎ ተዘግቷል። አንኳኳሁኝ….ዝም። መልሼ በሃይል አንኳኳሁኝ…ጎረቤቴ ሁሌም የሚለብሳትን ግራጫ ሹራብ እንደለበሰ ከፈተልኝ። አደባባይ ከወጡ እረጅም ጊዜ እንዳሳለፉ የሚያስታውቁትን ጥሮሶቹን እንደምንም ፈልቅቆ ሰላም አለኝ። በሩን ሳይከፍት መዋሉ ግራ ኣጋብቶኝ ልጠይቀው እንደመጣው ነገርኩት።ወደ ውስጥ እንድዘልቅ ጋብዞኝ ገባሁ፤ ለረጅም ጊዚያቶች ስከታተለው እንደቆየሁ፤ አኗኗሩና አድራጎቱ ሲገርመኝ እንደከረመ አጫወጥኩት። ወደ ውስጥ እንደገባሁኝ አትኩሮቴን የሳበው፤ ሁሌ ወደውጭ የሚጎትተው የስዕል ሸራው ነበር። በነጩ ሸራ ላይ፤ ትልቅ ክብ ተስሏል። ባዶ ትልቅ ክብ። ይህንን ለመሳል ነበር ዘወትር በርጩማው ላይ ተቀምጦ የነበረው?

“ዛሬ በሬን ዘግቼ ለመዋል ወሰንኩኝ፤ ከረጅም ጊዜ በኋላ” አለኝ “ለምን?” አልኩት “አንዳንዴ ቢጠበቁ የማይመጡ ነገሮች አሉ፤ በተስፋ ብቻ በርሽን እንዳገረበብሽ፤ የሚያስውሉሽ። ይመጡ ይሆን? እያልሽ እነሱ መንገድ ሳይጀምሩ ያንቺ ልብ ከቦታው ይጠብቃል። ሰው በተስፋ ብዙ ነገሮችን ቢያገኝም በተስፋ ደግሞ የሚያጣቸው ነገሮች አሉ። ላይመጡ የሚቀጥሩ አንዳንድ ምኞቶች እንዳሉ ታውቂያለሽ? ሰው በተስፋ ሊኖር ግድ ቢለውም ፤ ላይመጡ የሚቀጥሩ ተስፋዎችን ሲጠብቅ ግን ጊዜውን ማባከን የለበትም፤ ህይወትን በጥበቃ ማሰለፍ በኋላ ሊያስቆጭ የሚችል ውሳኔ ነው፤ መጠበቁን ጠብቂ፤ የቀጠርሽውን ምኞትና ተስፋ ግን በደንብ መርምሪ፤ መንገድ ያልጀመረውን ስንጠብቅ፤ በሰዓቱ የደረሰውን ችላ ስለምንለው። ቢያንስ ከእንደኔ አይነቱ ምስኪን አንዲት የምክር ጠብታ” አለኝ። “ስዕሉስ” አልኩኝ “የስዕሉን ሚስጥር” ጮክ ባለው ድምጹ፤ ያለወረቀት ግጥም ያነበንብልኝ ገባ ገርበብ ካለው በራፍ በርጩማ አስቀምጬ ስጠብቅ ነበረ ጭልጥ ባለ ሃሳብ በምኞት ሰምጬ መጠበቅ….መጠበቅ…….መጠበቅ ዝም ብሎ መጠበቅ ከበራፍ ላይ ሆኖ እንዳይደፈኝ ብዬ ሃሳብ እንቅልፍ ሆኖ አንዲት ስዕል ጀመርኩ በወረቀት ቁራጭ የጠበቅኩት መጥቶ በራፌን ስዘጋ፤ አብራ የምትቋጭ የጀመርኩት ስዕል አልተወሳሰበም፤ አልበዛም ጥበቡ አንድ ክብ ብቻ ነው፤ የስዕሌ ሃሳቡ የክቤን ጫፍ ይዤ ዝም ብዬ አከባለው በሬንም ገርብቤ እጠባበቃለው ብዙ ጊዜ ሆነ በሬንም ሳልዘጋ፤ እንዳንገረበብኩት ክቤንም ሳልከበው ክፍቱን እንደተውኩት ዛሬ ግን…….በራፌ ላይ ሆኜ ኑሮዬን አሰብኩት ይህን ያህል ጊዜ ከፍቼ የተውኩት የሚመጣ ካለ እያልኩኝ ነበረ አላፊ አግዳሚውን አይኔ እያማተረ ክፍቱን ያቆየሁት ያልቋጨሁት ክቤን ማድረስ አቅቶኝ፤ ጅምሩን ሃሳቤን ዛሬ ግን…..ጥበቃው ሰልቸኝ፤ የማይቋጭ ተስፋ የማይመጣን ማለም፤ መቃዠቱ ከፋ ጀምበሯ ስትጠልቅ፤ ሰማዩ ሲደማ በራፌ ተዘጋ፤ ተነሳ ብርጩማ ስዕል ተጨረሰ ክቡ ተከበበ ሊበር የነበረው ያ ምኞት አሞራ፤ ክንፉን ሰበሰበ! መቆረጥ ያለበት ተስፋ ሊኖር ይችላል፤ ጨለምተኛ ስለሆንን ሳይሆን፤ መተዋችን ለሌላ መልካም ነገር ነጻ እንድንሆን ስለሚያደርገን እንጂ።


76 views0 comments
bottom of page