top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“ከብቶች ሁሉ አንድ አይነት ሳር እየበሉ …”(በሚስጥረ አደራው)

Updated: Jun 9, 2019

“ከብቶች ሁሉ አንድ አይነት ሳር እየበሉ ፋንድያቸው ለምን ተለያያ?” ፣ ይህ አባባል ለከብቶች መንጋ ብቻም ሳይሆን ለሰዎች መንጋም የሚሰራ መሰለኝ። አንድ አይነት ትምህርት ቤት ገብተን፤ በአንድ አይነት መምህር ተምረን፤ በአንድ ክፍል ውስጥ ተቀምጠን፤ በስተመጨረሻ አንዳችን ከፍ ብለን ስንቆም ሌሎቻችን ግን ከጀመርንበት ፈቀቅ አንልም። ይህን ጥያቄ ስንጠይቅ የሰውን ልጅ የህይወት መስመሮች ሊቀይሩ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ በማሰብ ጭምር ነው። ሌሎቻችን የማናውቃቸው በእያንዳንዳችን ጎዳና ላይ የሚጋረጡ ውጣ ውረዶችን በመዘንጋት አይደለም። ነገር ግን ብዙ ጊዜ እኩል እድል ተሰጥቶን፤ በተመሳሳይ ሰዓት ፊሽካ ተነፍቶልን እያለ፤ ለምንድን ነው ውጤታችን የሚለያየው? እርግጥ ነው በውድድሩ አለም ሁሉም ሰው አሸናፊ ሊሆን አይችልም። ህይወት ግን እርስ በእርስ የሚፎካከሩባት የሩጫ ሜዳ ሳትሆን ሁሉም በገዛ ሜዳው እሮጦ ሁሉም በራሱ ሜዳ አሸናፊ ሊሆን የሚችልባት ቦታ ናት።

ከብቶች ሁሉ አንድ አይነት ሳር እየበሉ ፋንዳያቸው ለምን እንደሚለያይ ከአባባልነቱ በዘለለ እኔ በግሌ የማውቀውም ሆነ ያነበብኩት የለም። እንደው አባባሉ ከሰው ልጆች ህይወት ጋር ተመሳስሎብኝ ብዕሬን አስነሳኝ እንጂ። እኔ እንኳን በአጭሩ እድሜዬ አንድ አይነት ትምህርት ቤት ተምረን እኩል ሀ ሁ ያልን ልጆች አሁን በተለያየ የህይወት እርከን ላይ ሆነን ሳይ፤ ልዩነቱ ምን ላይ እንደሆነ ለማወቅ ጓጓሁኝ። የኑሮ እርከን ብዬ ስናገር፤ ስኬት በግል መመዘኛ የሚመዘን መሆኑን በመዘንጋት አይደለም። ሆኖም ተመሳሳይ እድል ተሰጥቶን፤ በእኩል ሰዓት ፊሽካ ተነፍቶልን፤ አንዳንዶቻችን ለምን ከመንገድ እንቀራለን? ተመሳሳይ እድል ገጥሞን ውጤታችን ለምን ይለያያል? አንድ አይነት የኑሮ ሳር ግጠን ለምን ከእኛ የሚወጣው ነገር የተለያየ ሆነ?

ከታች የዘረዘርኳቸው ነጥቦች ጥቂቶችን ከብዙሃኑ ከሚለዩዋቸው ባህሪዎች ውስጥ ወሳኞቹ ናቸው። አሸናፊዎችን ከብዙሃኖቻችን ነጥረው እንዲወጡ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ነገሮች ቢኖሩም የሚከተሉት ግን ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

1) አሸናፊዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ የምንፈልገውን እንደ አለማወቅ በዚህ ምድር ላይ እንድሜያችንን የሚበላ ምንም ነገር የለም። ብዙዎቻችን እራስን ፍለጋ በሚለው ፈሊጥ አቅጣጫው እንደጠፋበት መርከብ በባህር ላይ እንቀዋለላለን። የምንፈልገውን ባለማወቃችን የማንፈልገውን ኑሮ ለመኖር እንገደዳለን። እዚህ ላይ ግን ልብ ልንለው የሚገባና ብዙዎቻችን የተሳሳተ መስመር ውስጥ የሚከት አስተሳሰብ አለ። ይህም እራስን ፍለጋ በሚል ፈሊጥ የብዙ ሰዎች እድሜ ይባክናል። ብዙዎችን የሚያስማማው የእራስን የማግኘት ትርጉም ፤ የሚያስደስተንን ነገር ማድረግ ነው። አለን ዋትስ የተባለ ሊቅ በአንድ ወቅት ለወጣቶች እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር

“ብዙ ወጣቶች እራሳቸውን እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው እንዳስረዳቸው ይጠይቁኛል። በተለይ ከከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት ወጥተው አዲስ የኑሮ ምዕራፍ ለመጀመር የተዘጋጁ ወጣቶች በህይወታቸው ምን መምረጥ እንዳለባቸው ስለማያውቁ እርዳታ ይጠይቁኛል። የኔ መልስ እንዲህ ነው ገንዘብ ቅድሚያ ባይሰጠው ምን ማድረግ እንደሚያስደስታቸው እጠይቃቸዋለው? ገንዘብ ቦታ ባይኖረው ጊዜያቸውን ምን በማደረግ ማሳለፍ እንደሚሹ ሲነግሩኝ እራሳቸውን በዛ ውስጥ እንደሚያገኙት መክሬ እሰዳቸዋለው።” ብሏል።

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን አንድ ነገር አለ። በተለይ በእኛ አገር ገንዘብን የሚያስገኝን ነገር ትተን ተሰጥዎን በነጻ ልኑር ማለት ዘበት ነው። ስለዚህ አንዴ የምንፈልገውን ነገር ካወቅን በኋላ ያንን ተሰጥዎ ወደ ገንዘብ የምንለውጥበትን መንገድ መመርመር አለብን። ባጠቃላይ የምንፈልገውን ማወቅ፤ በነፍሳችን ውስጥ የተለየ ጉልበት እንዲኖረን ያደርገናል።

2) አሸናፊዎች ልዩ መሆንን አይፈሩም- እውነት እንነጋገርና ልጆች ሆነን እንደው ልዩ በመሆናቸው ብቻ የምናሾፍባቸው እኩዮቻችን እንደነበሩ እናስታውሳለን። ከብዙሃኑ ጋር አብረው ባለመጓዛቸው የተወቀሱ፤ የተሾፈባቸው ልጆች ናቸው በስተመጨረሻ የሩጫው አሸናፊ ሆነው የምናያቸው። ሮል ሞይ የተባለ ጸሃፊ ሰዎች በህይወታቸው ስኬታማ እንዳይሆኑ ከሚያደርጓቸው ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ልዩነትን መፍራትና ብዙዎች በሄዱበት መንገድ ለመሄድ መሞከር ወይም ብዙሃኑን መምሰል እንደሆነ ይናገራል።

3) አሸናፊዎች የራሳቸው አነቃቂዎች ናቸው- ብዙዎቻችን የሚያነቃቃን ነገር እንፈልጋለን። ለምሳሌ ልጅ ሆነን እንኳን አንዳንድ ተማሪዎች የቤት ስራቸውን የሚሰሩት ወይ የአስተማሪውን ቁጣ ፈርተው አልያም የቤተሰብን ግርፊያ ፍራቻ ነው። ጥቂት ተማሪዎች ግን መምህሩ ኖረም አልኖረም፤ ቤተሰብ ተቆጣጠራቸውም አልተቆጣጠራቸውም የቤት ስራቸውን መስራታቸው አይቀርም። እንደዚህ አይነቶቹ ተማሪዎች ናቸው በኋላ በህይወታቸውም ለኑሮዋቸው ሃላፊነትን መውሰድ የሚችሉት። እንደዚህ አይነት ሰዎች የሌላው ማነቃቂያ ሳይሆን የራሳቸው ፍላጎት ነው የኑሮዋቸው መቅዘፊያ።የመጀመሪያ ነጥብ ማለትም ፍላጎትን ማወቅ ከዚህ ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው። የምንፈልገውን ነገር ስናደርግ ከራሳችን ፍላጎት ውጪ ማነቃቂያ አያስፈልገንም።

4)አሸናፊዎች ምክንያት ደርዳሪዎች አይደሉም- የብዙዎቻችን ውድቀት ምክንያት ይህ ነው፤ የምንፈልገውን ላለመሆናችን ምክንያት መደርደር እንፈልጋለን። ለውድቀታችን እራሳችንን እንደመመልከት የስህተታችንን ሚስጥር ሌሎች ላይ ለመፈለግ እንጥራለን። ሃላፊነት መውሰድ ስለሚሳነን፤ ልክ እንደጦጣዋ ተረት “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ማለት እናበዛለን። ስኬት ማለት ባህሪ ነው። ስኬታማ ሰዎች በየእለቱ በሚያከናውኗቸው ነገሮች ላይ ሙሉ ልባቸውን እና ትኩረታቸውን ሰጥተው ነው። ባይሳካላቸው ስህተቱን ሌላው ላይ በመፈለግ ጊዜያቸውን አያባክኑም።

5) አሸናፊዎች ተስፋ አይቆርጡም- ተስፋ የህይወት ሁሉ እስትንፋስ ነው። ምንም እንኳን እኩል እድል ተሰጥቶን፤ በተመሳሳይ ሰዓት ፊሽካ ተነፍቶልን ጉዞ ብንጀምርም ብዙዎቻችን ተስፋ በመቁረጥ ከመንገድ ቀርተናል። ምንም እንኳን እሩጫው ቢከብድም ተስፋ በውስጣቸው የሰነቁ ሰዎች በቀላሉ ከመንገዳቸው አይገቱም።

ከላይ የተዘረዘሩት አምስት ነጥቦች ከብዙዎቹ የአሸናፊ ሰው ባህሪዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከብቶች አንድ አይነት ሳር ግጠው ፈንዳያቸው እንደሚለያይ ሁሉ፤ የሰው ልጆችም ተመሳሳይ እድል ተሰጥቷቸው የተለያየ ቦታ ይወድቃሉ። ምንም እንኳን ምክንያቶቹ ተዘርዝረው ባያልቁም፤ ከላይ የሰፈሩት አምስጥ ነጥቦች ግን አንኳሮቹ ናቸው፤ በእርግጠኝነት እራሳችንን እንድንፈትሽ ያደርጉናል።


በሚስጥረ አደራው

141 views0 comments

Comments


bottom of page