top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"ለሰው ጉድጓድ አትቆፍር ከቆፈርክም አታርቀው ማን እንደሚገባበት አይታወቅምና"


"ለሰው ጉድጓድ አትቆፍር ከቆፈርክም አታርቀው ማን እንደሚገባበት አይታወቅምና!የሚለው አባባል ደስ የሚያሰኝ አባባል ነው። እንጀራቸውን በክፋትና በቅጥፈት ሲጋግሩ የኖሩ ሰዎች ለማብሰል ሲሉ ባነደዱት እሳት የተገረፈው ሁሉ"የሥራህን ጀባ!"ሲላቸው ይኖራልና በተበተቡት መጠለፋቸው፣በቆሰቆሱት መማገዳቸው፣ባቆሩት መስመጣቸው አይቀርም!!"ለክፉ ሰው የራሱ ክፋት ይበቃዋል!"እንደተባለው!!እንደ ክብሪት እንጨት የወጡበትን ስለሚረግጡ፣የበሉበትን ወጪት ስለሚሰብሩ፣በክፉ ጊዜ ያሻገራቸውን ምርኩዝ ስለሚጠየፉ እፉኝቶች ምንዳ ነው የማወራው የዘገዬ ቢመስልም ስለማይቀረው!

በአንድ ቤተ መንግስት ውስጥ ታዋቂ የንጉስ አዝናኝ ነበር።ይህ ሰው ሁሌም ለንጉሱ የሚናገረው አባባል አለ፦"ንጉስ ሆይ ለጥሩ ሰው ለጥሩነቱ ጥሩ ነገር ያድርጉለት፣ለመጥፎ ሰው ግን መጥፎ ተግባሩ ትበቃዋለች!"የሚል። ታድያ ንጉሱ ለዚህ አዝናኝ የሰጡት ከበሬታ ምቾት የነሳው ሌላ ሰው ይህን ቀረቤታቸውን ለማደፍረስ ይፈልግና ወደ ንጉሱ በመሄድ "እገሌ የሚባለው ሰውዬ ንጉሱ መጥፎ የአፍ ጠረን አላቸው እያለ ያስወራል" አላቸው። የነገራቸውን ነገር እንዴት ማረጋገጥ እንደሚችሉ ሲጠይቁትም "ይጥሩትና ሲቀርብዎ እጁን በአፍንጫው ላይ ካደረገ የተናገርኩት እውነት ነው ማለት ነው።" በማለት መከራቸው።

ንጉሱም "እሺ አንተ ሂድ እፈትነዋለሁ" አሉት።

ተንኮለኛው ሰው ወደ ቤቱ ሄዶ አዝናኛቸውን ነጭ ሽንኩርት የበዛበት ራት ጋበዘው። (ያበላህ ሁሉ ወዳጅህ አይደለም!) አዝናኙም ከግብዣው በኋላ እንደተለመደው ንጉሱን ሊያጫውት ሄደና "ንጉስ ሆይ!ለጥሩ ሰው ጥሩነቱ…ማለት ሲጀምር" ና ወደኔ ቅረብ!" አሉት። እሱም ነጭ ሽንኩርቱ እንዳይሸታቸው ሰግቶ አፉን በእጁ ይዞ ቀረባቸው። ንጉሱ ይህንን ሲመለከቱ የሰሙት ነገር ትክክል እንደሆነ በማሰብ ለአገረ ገዣቸው"ይህንን ደብዳቤ ይዞ የሚመጣውን ሰው ወዲያው ቆራርጠህ ግደለው! "የሚል ደብዳቤ ፅፈው አዝናኛቸውን እንዲያደርስ ላኩት።አዝናኙ መንገድ ሲጀምር ተንኮለኛውን ሰው ያገኘውና ወዴት እየሄደ እንደሆነ ሲጠይቀው" ይህ ሽልማት እንዲሰጠኝ ንጉሱ ያዘዙበት ደብዳቤ ነው"ይለዋል በሙሉ እምነት። ተንኮለኛውም "እባክህ አንተ ደግሞ እሱን ለኔ ሸልመኝ"ብሎ ሲማፀነው ይፈቅድና ይሰጠዋል።

ተንኮለኛው ለሽልማቱ እንደጓጓ አገረ ገዢው ጋር ሲደርስ በደብዳቤው ላይ ያለው ትክክለኛ መልእክት ተነገረው።ያኔ "ይህ ደብዳቤ የተሰጠው ለ‘ኔ አልነበረም፣እባካችሁ ጉዳዩን አጣሩልኝ!" እያለም ለመነ።እነሱ ግን ሥራቸው የንጉሱን ትእዛዝ ያለ ምንም ማወላወል መፈፅም እንደሆነ አሳውቀው ገደሉት።

የንጉሱ አጫዋች ወደ ቤተ መንግስቱ ሲመለስ ንጉሱ በመገረም"ደብዳቤውን ምን አድርገህ ነው የመጣኸው?"በማለት ጠየቁት። እሱም ሂደቱን በሙሉ ነገራቸው፣ ስለሰሙት ወሬ አጫወቱት፣ እውነታውም ታወቀ!! ንጉሱም "አንተ እውነቱን ተናግረሃል ወደ ስራህ ተመለስ ተንኮለኛውም በተንኮሉ ተብቃቅቷል!" በማለት አሰናበቱት!!

55 views0 comments
bottom of page