top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

በጉራጌ “ክልል ልሁን” ጥያቄ ላይ ውስጣዊ የመከፋፈል አደጋ ምንጭና ብቸኛው መውጫ መንገድ (በላይ ነኝ ዶቢ ክስታኔ)


በጉራጌ “ክልል ልሁን” ጥያቄ ላይ ውስጣዊ የመከፋፈል አደጋ ምንጭና ብቸኛው  መውጫ መንገድ (በላይ ነኝ ዶቢ ክስታኔ)

በጉራጌ ክልል ልሁን ጥያቄ ላይ ውሃ የቸለሰበት ውስጣዊ የመከፋፈል አደጋ ምንጩ ከምንድነው የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ በግራ አጋቢነት መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን የዕይታ እና የዕምነት መከፋፈል ወደ ህዝባዊ ዕይታና እምነት የሚለጥጡም አይጠፉ ይሆናል፡፡ እውነታው ግን ከወዲህ ነው፡፡ የጉራጌ ህዝብ ቀደም ሲል በነበሩ የደርግና ቀደምት የአገዛዝ ስርዓቶች አሁን ምስራቅ ጉራጌ በሚል የሚጠቀሱት ወረዳዎች ያሉበት ክፍለ ህዝብ በቀድሞው ደቡብ ሸዋ አስተዳደር በሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ ውስጥ ይተዳደር ነበር፡፡ አሁን ምዕራብ ጉራጌ ተብሎ የሚጠራው ክፍለ ህዝብ ደግሞ በጨቦና ጉራጌ አውራጃ አስተዳደር ወሰን ውስጥ ይገኝ የነበረ ነው፡፡ ኢህአዴግ የደርግን መንግስት ጥሎ የወሰንና አስተዳደር ለውጥ ሲደረግ እነዚህ አንድ ነገር ግን በተለያየ የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የነበሩ ሁለት ክፍለ ህዝቦች የአሁኑ የስልጤ ዞንን ጨምሮ ወደ አንድ ዞን ተጠቃለው ጉራጌ ዞን የሚል መጠሪያ ያዙ፡፡ ቀደምት የሂደቱ እና የአደረጃጀቱ አርክቴክቶች እንደሚሉት ከሆነ ይህ አዲስ ዞን ሲመሰረት ከዞን መቀመጫነት ጋር በተያያዘ በወቅቱ በነበረው ድርጅትም (ጉህአዴን) ሆነ እንደ ዞን አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ያለመግባባት ተከስቶ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ ስልጤ ዞን ውስጥ ያሉ ወረዳዎች፣መስቃንና ማረቆ ብሎም ሶዶ ወረዳዎች ውስጥ የነበሩ የመንግስትና የድርጅት አመራሮች በአስተዳደራዊ አመቺነትና ማዕከልነት የዞኑ መቀመጫ ቡታጅራ መሆን አለበት ሲሉ ሞግተው በድርጅትም ጭምር በአብላጫ ድምጽ ውሳኔ አግኝቶ ነበር፡፡ ይሁንና በወቅቱ በህዝባዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ከማመን ይልቅ መንደርተኝነት ያጠቃቸው የነበሩ የምዕራብ ጉራጌ ካድሬዎች ይህ ውሳኔ ተላልፎ ሳይጠናቀቅ መረጃ አሾልከው በመስጠት የወልቂጤ ከተማ ህዝብ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጣ አደረጉ፡፡ በዚህም ምክኒያት በ‹‹እናረጋጋው›› ሰበብ የድርጅት ውሳኔ ተሸራርፎ የግለሰቦች ውሳኔ ተግባራዊ ሆነ፡፡ ወልቂጤም የዞኑ ማዕከል ሆና ቀጠለች፡፡ ይህ ሁኔታ እየዋለ እያደረ ቅሬታ እየፈጠረ መጥቶ የዞኑ መቀመጫ ለዞኑ ህዝብ አስተዳደራዊ አመቺነት እንደሌለውና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ወደ ምዕራብ ያደላ እሳቤ እንዲከረከም ብዙዎቹ የምስራቅ ጉራጌና የአሁኑ የስልጤ ዞን አመራሮች በተናጠል እና በቡድን ሞገቱ፡፡ ይሁን እንጂ ለሚነሱ ቅሬታዎች መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ እየነጠሉ መምታትን እና እርስ በእርስ ማባላትን እንደስትራቴጂ በመጠቀም ብዙዎችን ከትግል ሜዳው አስወገዱ፡፡ በዚህ ሁኔታ ቂም እየቋጠረ እና መፍትሄ እየባጀ የመጣው የስልጤ ህዝብ የማንነት ጥያቄ በማንሳት ከዚህ የሴራ ፖለቲካ የሚያመልጥበትን ስልት ነደፈ፡፡ በብዙ መሻትና ውጣ ውረድም እሳቤውን ዕውን አድርጎ የራሱን ዞን መሰረተ፡፡

የተቀሩት የምስራቅ ጉራጌ ዞን ወረዳዎች ግን ከስልጤ እምቢተኝነት መወለድ ሊጋሩ ይችላሉ የሚለው እንደ ተሞክሮ ተወስዶ ጠንካራ አመራር እንዳይወጣላቸው፣ ጠያቂ ትውልድ እንዳይፈጠር በድርጅትና መንግስታዊ መዋቅር በተሰራ ሰንሰለት ይቀጠቀጥ ተያዘ፡፡ ሲያሻቸውም ትርፍ ያስገኝልናል ያሉትን የሴራ ፖለቲካ በመጠቀም አብሮ የኖረ፣የተዋለደና እንዳይለያይ የተጋመደን ህዝብ ያባሉ ያዙ፡፡ መስቃን ከዶቢ ክስታኔ ማረቆ ከመስቃን ሶዶ ክስታኔን እርስ በርስ ቀቤናን መግፋት ወለኔን መበደል አስተዳደራዊ በደል ማድረስ የለት ተግባራቸው ሆነ። በአካባቢው ላይ ለማልማት ጥያቄ የሚያቀርቡ አልሚዎችን ማሰናከል፣ በአካባቢው ባለሃብቶች ሊሰራ የታቀደን የልማት ስራ ካለ ይሉኝታ ማደናቀፍ፣ በክፍለ ህዝቡ አካባቢ ይሄ ነው የሚባል ልማት ያለማጽናት፣ ነባርና ብቃት እየለበሱ የሚወጡ አመራሮችን ሲመች ሁኔታን አስታኮ መምታት ሳይመች ደግሞ በዕድገት ስም ትርጉም የለሽ ቦታ ላይ መደቦ ሚና ማሳጣትን እንደ አዋጭ ስትራቴጂ ይዘው ያስተዳደሩ ነበር ከሚባል ይልቅ ይገዙ ጀመር፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የኢህአዴግ የአገዛዝ ስርዓት እየከሰመ መምጣትን ተከትሎ በደቡብ ክልል ውስጥ ሲዳማን ጨምሮ በወላይታ እና በሌሎችም ጭምር የክልል እንሁን ጥያቄ እዚህና እዚያ ይነሳ ጀመር፡፡ በወቅቱ ‹ሲዳማ ክልል ከሆነ እኛም እንሆናለን› በሚል ሁሉም ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄ ማንሳታቸው በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የጉራጌ ዞን ምክር ቤትም ነባር ችግሮቹን ሳይፈታና ቂምና ቋጠሮዎቹን ሳይሽር እንደሁሉም ዞን ምክር ቤቶች ወስኗል፡፡ ይህ ውሳኔ የተላለፈበት ጊዜ በደቡብ ክልል ስር ያሉ ሁሉም ዞኖች ክልል የጠየቁበትና ሁሉም ወደየ አፎቱ የተመለሰበት ጊዜ እንደነበር ሳንረሳ መንግስት ወዳስቀመጠው የችግር መፍቻ መንገድ እናምራ፡፡ የሲዳማ ክልል እንሁን ጥያቄ ሳይጠናቀቅ መንግስት የደቡብ ክልል እንደምን ባለ የክልል መዋቅር ቢደራጅ ይሻላል የሚለውን እንዲያጠኑ ከሁሉም የክልሉ ብሔሮች የተወጣጡ ምሁራንን ሰየመ፡፡ ምሁራኑ ብዙ ከወጡና ከወረዱ በኋላ መፍትሄ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ አቀረቡ፡፡ በወቅቱ ይህ ጥናት ለሚመለከታቸው ሁሉ በተለያየ የመንግስትና የድርጅት አደረጃጀት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በወቅቱ ከሲዳማ ክልል ተወላጆች በስተቀር ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ አጥኚው ቡድንና መንግስት ባስቀመጡት አጀንዳ ላይ መግባባት ተደረሰ፡፡ እነሆ ወደ አደረጃጀትና ክልል ምስረታ የተሸጋገረው የአጥኚዎች ምክረ ሃሳብ ከሲዳማ ጀምሮ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ክልሎች ዕውን አድርጓል፡፡ በቀጣይነት ሲጠበቁ የነበሩት ወላይታ፣ጋሞ፣ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና ጌዴኦ ዞኖች ልዩ ወረዳዎችን ጨምሮ በአንድ ክልል ጣሪያ ስር ለመሰባሰብ ወስነዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁናቴ ከወዲህ ሃዲያ ስልጤ፣ከምባታ፣ሃላባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ጉራጌ ዞንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአንድ ክልል እንደራጅ ሲሉ በየምክርቤቶቻቸው ወስነዋል፡፡ በስተመጨረሻም ሲጠበቅ የነበረው የጉራጌ ዞን በሁለት የአስተሳሰብ ጫፎች ላይ ቆሞ በምዕራብ ጉራጌ ካድሬዎች የሴራ ፖለቲካ በታጀበ የድምጽ ብልጫ የቀደመ የክልል እንሁን ጥያቄ በውስን ድምጽ ልዩነት ወስኗል፡፡ እንግዲህ በዞኑ ውስጥ በምስራቅ እና ምዕራብ ሁለት ጫፍ የመፈጠራቸው መነሻዎች ከላይ ከመግቢያችን ያነሳናቸው የፖለቲካ ጭቆናዎች፣ አስተዳደራዊ ምቹነት ያለው ማዕከል ያለመመስረትና የመልካም አስተዳደር ዕጦቶች መሆናቸውን ዋነኛ ጉዳያችን አድርገን ይዘን ልዩነቱ በዚህ ደረጃ የህልውና ጉዳይ ሆኖ የወጣበትን ሚስጥር እንመርምር፡፡

የዞኑ ማኅበረሰብ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በአብላጫ ድምጽ ውሳኔዎችን አሳልፎ እና ለውሳኔዎቹ ተገዥ ሆኖ ያውቃል፡፡ ይህን ውሳኔ የህልውና ጉዳይ አድርጎ የወሰደበት ሚስጥር አንድም ‹በአብሮነት እንደራጅ› ሲሉ ከወሰኑት ብሔሮች ጋር ያለው ተዛምዶና የጠበቀ ቁርኝት በስያሜ እንጂ በአኗኗር ዘይቤ፣ በባህል፣ በፖለቲካና የማህበረሰብ ተመሳስሎሽ ስላላቸው፤ ሁለትም በምዕራብ ጉራጌ ካለው የፖለቲካ ሴራና ጭቆና ለማምለጥ ሁነኛ ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶች የዞኑ ምክር ቤት የምዕራብ ጉራጌ ድምጽ የተጫነው ውሳኔ ምስራቅ ጉራጌ ያሉ ወረዳዎች እየቀለበሱ ያሉበትን መንገድ ‹ጉራጌ ተበተነ› የሚል ድምዳሜና አውድ አስይዘው ሲተነትኑ ይታያል፡፡ እውነታው ግን ጉራጌ ጉራጌነቱን ነብር ዥንጉርጉርነቱን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የማይተው መሆኑን ነው፡፡ ጉራጌ በዘመነ ደርግ በነበረው የአስተዳደር መዋቅር በተለያዩ አደረጃጀቶች ኖሯል፤ በዘመነ ኢህአዴግም በአብሮነት ኖሯል፡፡ ወደፊትም ይኖራል:: በጉራጌ ዞን ውስጥ አንዱ የጉራጌነት ክብር አልባሽ ሌላው ለባሽ የለም፡፡ የጉርጌነት ተቆርቋሪና በማንነቱ ላይ ግዴለሽነትን ለብሶ ማንነቱን የሚሸጥም የለም:: በፖለቲከኞች የሚዘወረው አዳፋ ተግባርም በሁለቱም አካባቢ ነዋሪ ህዝቦች ዘንድ ችግር ሆኖ አብሮነትን የሚያሻክር አይደለም፤ ምክኒያቱም ህዝቡን ከሴራ ፖለቲካው ሽንቁር ይልቅ የሚያሰናስለው ይበዛልና ነው:: ጎጃም በምዕራብና በምስራቅ፣ ጎንደር በሰሜን በደቡብና ምዕራብ፣ ወሎ በሰሜን እና በደቡብ እንደሚኖር ሁሉ ጉራጌም በሚያመቸው አደረጃጀት ውስጥ ተካሎ ማንነቱን ይዞ ይቀጥላል:: በአብሮነት መኖር አስተዳደራዊ አመቺነት ሲኖር መልካም ቢሆንም በሌለበት ሁኔታ ግን የግድና የህልውና ማስጠበቂያ ብቸኛ መንገድ አይደለም፡፡ ‹እኔ በምልህ እንጂ አንተ በምትለው አትኖርም› ይሉት እሳቤ ለማንም እና ለምንም አይበጅም:: ይልቁንም በውሳኔው ላይ የተፈጠረውን የድምጽ ልዩነት ተከትሎ አንድን ክፍለ ህዝብ በባንዳነት የመፈረጅ አዝማሚያ ሊያስከትለው የሚችለውን ትውልድ ተሻጋሪ ቁርሾ በአደገኛነቱ ሊታይ የሚገባ ነው:: መጪው ጊዜ በብስለትና ‹የእኔ ብቻ ፍላጎት ይከበር› ከሚል ያዘመመ እሳቤ ርቀን ማሰብ ካልቻልን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የምዕራብ ጉራጌ ወገኖቻችን ዕጣ ፈንታ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከብሽሽቅ ወጥቶ ሰከን ብሎ ማሰብ፣ ከስሜታዊነትና ዘላቂ ገዢነት ወጥቶ ስለ እኩልነት፣ በአብሮነት ስለመኖር፣ በቂም እና ጥላቻ የተሞላውን ቁስል መሻር ላይ ያተኮረ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በዞኑ ውስጥ ካሉ ክፍለ ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ከስልጤ ህዝብ ጋር የአብሮነትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፈን የሚያስችል የጋራ ውል ማሰር፣ ዳግም ቂም እና ጎሪጥ መተያየት ላይኖር በ‹‹ጉዳ ›› በ‹‹ሴራ›› ወይም እንደ ጎጎት አይነት የቃል ኪዳን ውል ማሰር ያሻል፡፡ የጉራጌን ላዕላይነት አስቀጥሎ የሚጓዘው እሳቤ እና ብቸኛው “የማርያም መንገድ” ይኼው እና ይኼው ብቻ ነው፡፡ ከመንግስት ጎን በመቆም በአብሮነትና ወንድማማችነት ጉዞ ወደ ደቡብ ሸዋ


በላይ ነኝ ዶቢ ክስታኔ

102 views0 comments
bottom of page