top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

አለመግባባትን በውይይት ማሸነፍ የሚችሉባቸው 9 መንገዶች


ትዳርን ጨምሮ በማንኛውም ግንኙነትና ወዳጅነት በነገሮች አለመግባባት፣ የሃሳብ ልዩነት ማስተናገድና መቃቃር ያጋጥማል። የስነ ልቦና ባለሙያዎች ደግሞ በዚህ ወቅት የሚኖርን አለመግባባት እንደ ደካማ ጎን ቆጥሮ #ልዩነትን ማስፋት እንደማይገባ ይናገራሉ። በሰከነ መንገድ መወያየትና የእኔ ሃሳብ ብቻ ገዥ ይሁን ማለትን በማስወገድም ለልዩነት መፍትሄ መፈለግንም ይመክራሉ። ከዚህ በታች ያሉት ደግሞ በየትኛውም ግንኙነት ሊከሰት የሚችልን ልዩነት በማስወገድ አለመግባባትን ማሸነፍ የሚችሉባቸው መንገዶች ናቸውና ያንብቧቸው።


1 – የፊት ለፊት ውይይት ማድረግ መቻል፦

አብዛኛዎቹ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ባይግባቡና የሰፋ የሃሳብ ልዩነት ሲኖር መራራቅና አለመገናኘት ወይም አለመወያየትን ይመርጣሉ፤ ይህ ግን ጤናማ አካሄድ አይደለም። በኩርፊያ ተራርቆ በጽሁፍ መልዕክት ከመላላክ ይልቅ በአካል ባይሆን እንኳን እንደ ኢንተርኔት ያሉ የመገናኛ መንገዶችን በመጠቀም #እየተያዩ መወያየት መልካም ነው፤ ይህም የተሻለ የሃሳብ መናበብ ለመፍጠር ይረዳል።

2 . ለውይይታችሁ የተሻለ ጊዜና ቦታ መምረጥ፦

የበዛ የሃሳብ ልዩነትና አለመግባባት እንደመፍጠራችሁ መጠን በሰከነ መንገድ ለመወያየትና ለመመካከር የተሻለ ጊዜና ቦታ መምረጥ ይገባል። ቦታና ጊዜው ፊት ለፊት ተናባችሁ በአግባቡ ልዩነትን ለመፍታና ለመወያየት በሚረዳ መልኩ ሊሆን ይገባል።

3. ጠቃሚውና ዋናው ነጥብ ላይ ማተኮር፦

በውይይታችሁ ወቅት ለልዩነታችሁ #መነሻ በሆነውና ባላግባባችሁ ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮር። ይህ መሆኑ የተሻለ በማተኮር የሃሳብ ልዩነታችሁን ለማስታረቅ ይረዳችኋል።


4 . ሌሎችን አለመውቀስ፦

ምንጊዜም ቢሆን ለተፈጠረው አለመግባባት “#እኔ” ብላችሁ ነገሮችን መጀመርና በዚያው መጠን መወያየት ይኖርባችኋል። ይህ የሆነው በአንተ/በአንች የሚል አካሄድ መኖሩ ለውይይታችሁ ጠቃሚ አይሆንምና ተፈጥሮ ለነበረው ነገር ከራስ ጀምሮ የጋራ ሃላፊነት በሆነ መንገድ ልዩነቱን መፍታት።


5 . ሌሎች ሰዎችን ማድመጥ፦

በውይይታችሁ ወቅት ስለተፈጠረው አለመግባባት #ያኛው ግለሰብ የሚለውን ነገር በአግባቡ መስማትና ማዳመጥ ይኖርባችኋል። ይህን ሲያደርጉ አንድም እርስዎ ያላስተዋሉትን የእርስዎ ችግር እንዲመለከቱ ያደርግዎታል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ነገሮችን ተመልክተው በውይይትዎ ተቀባይነት ያለው ሃሳብ እንዲያቀርቡም እድል ይፈጥርልወታል። ከዚህ በመነሳትም አለመግባባቱን ለመፍታት ባደረጉት ውይይት አሸናፊ ሃሳብ የሚያቀርቡበትን እድልም እንዲያገኙ ይረዳዎታል።

6. ሌላኛው ግለሰብ ሃሳቡን እንዲያቀርብ ማድረግ፦

በተቻለ መጠን ለነበረው ችግር የአንዳችሁ ሚና የጎላ ቢሆንም እንኳን እርስዎ ቀዳሚ ሆነው ወደ ጉዳዩ መግባት አይኖርብዎትም። ከእርስዎ ጋር የሚወያየው ሰው ጉዳዩን አንስቶ፥ ነበረ ባለው ጉዳይ ያለውን ሃሳብ እና ቅሬታ እስከሚገልጽ መጠበቅ መልካም ነው። ይህ ሲሆን እርስዎ በጉዳዩ ላይ የራስዎን ሃሳብ በምን መልኩ ማቅረብ እንዳለብዎት ጠቋሚ አቅጣጫ ያገኛሉ። 7. ለማጥቃት አይሞክሩ፦

በውይይታችሁ ወቅት የትኛውንም ያክል አለመግባባት ቢኖር እንኳን የቃላትም ሆነ የአካል ጥቃት አለማድረስ ይመከራል። ሁለቱም እርምጃዎች መፍትሄ እፈልግለታለሁ ያሉትን ነገር ወደ ባሰ ጣጣ ይከተዋልና ሁል ጊዜም ረጋ ብለው በትዕግስት ነገሮችን ለመፍታት ይሞክሩ።

8 . አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረብ፦

እሱን/እሷን አድምጠው ከጨረሱና ከተወያዩ በኋላ ምናልባት አሁንም ልዩነት ሊፈጠር ስለሚችል ሌሎች መንገዶችን ያስተውሉ። ይህን ሲያደርጉ ምናልባትም እርስዎ ይቅርታ ጠያቂም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይሁን እንጅ ከዘለቄታዊ ግንኙነት አንጻር ሁለታችሁንም የሚያስማማ አስታራቂ ሃሳብ ማቅረብና በዚያ መልኩ ልዩነቱን መፍታት። ይህ አካሄድ ቢያንስ ቢያንስ በስነ ልቦና እርስዎን አሸናፊም ያደርግዎታል።

9 . የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ፦

ምናልባትም እርስዎ ያቀረቡትና ያሉት ሃሳብ ጠቃሚና አስፈላጊ ቢሆንም እንኳን ይህን ሃሳብዎን ከሌሎች ሰዎች አንጻር ማየትና መገምገም ይልመዱ። የቱንም ያክል ጠቃሚ ቢሆንም ትንሽ ምቾት ያልተሰማው አካል ካለ ወደ ላይኛው ሃሳብ መመለስና አስታራቂና ቢያንስ ሊያግባባ የሚችል ሃሳብን ማቅረብ። በመጨረሻም በእነዚህ መንገዶች ተጠቅመው የተደረገውን ውይይት በአሸናፊነት መንፈስ አጠናቀው ልዩነትዎን ካስወገዱ በኋላ፥ መልካምነት ሊለይዎት አይገባም። ነገሮችን በሰላም ከፈታሁና ከከወንኩ በኋላ ከዚህ/ከዚች ሰው ጋር ምን አደርጋለሁ በሚል መራቅ ሳይሆን በመልካምነት ወዳጅነትን ማዝለቅና ማጠንከር ይገባል። ከላይ የተጠቀሱት የመፍትሄ ሃሳቦች በፍቅር፣ በትዳር፣ በጓደኝነት አልያም በስራ አጋርነት ላይየሚከሰቱ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በአሸናፊነት በመወጣት የነበረን ግንኙነት ለማደስ የሚረዱ ናቸው።


ምንጭ - FBC

59 views0 comments
bottom of page