top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች (ክፍል - 13)


93. ዕድሜውን ሁልጊዜ ከእኔ ከተጣላ

ደንዳናው ኢማኑ ይሆናል ነጠላ

ባዶውን እንዳቀር ተጭኖ እየበላ

ቃልቻን ተው በሉት ጠንብቶ እንዳተላ

እንዴት ይሐስደኝ ጠጥቶ እየበላ?


94. ቃልቻን ተው በሉት ደም ሳላስለቅሰው

እባክህ ጌታዬ አታጣላኝ ከሰው

ሳይደርሱት ይደርሳል መቼም የተላሰው

ኢማኑ እንደ እንቁላል ፈርጦ የፈሰሰው

በየደረሰበት ቀልብ እየጠበሰው::


95. ሸዋ መርዙን ገዛ መሪውን ሳይተካ

ወያኔ አስፈራርቶት ንጉሥ እንዳይተካ

መዝረፍ እንዲመቸው ቦታና ፈረንካ

እንዴት ሰው በአገሩ ደም ለውሶ ያቡካ?

ጥይት እህል ሆኖ ሐበሻ ላይ ቦካ::


96. ቦታና መሬቱን ከተወሰደበት

ወዲያው መዓት ይወርዳል እርስ በርስ ጦርነት

በአማራ በእስላም ይገባል ድህነት

በተለይ አሥመራ ትሆናለች ዱቄት

ሸዋ ጠላት ገዛ ጥይት እረከሰበት::


97. ተፈሪን አውርደው ተፈሪ ከገዛ

ለትንሽ ቀን እንጂ እጅግም አይገዛ

ለዕለት ተጠንቀቀው አይምሰልህ ዋዛ

በጉልበት ካልሆነ በፍቅርም አይገዛ

ኋላ ግን ሟች ናቸው ነገሩ ከበዛ::


98. መሳፍንት ከሞተ በሸዋ መዲና

ችግር ይፈጠራል አገርም አይቀና

ሐበሻ የዚያን ቀን አያገኝም ጤና

መለፍለፍ ነው እንጅ አዋጁም አይጠና

በለው ቶሎ አይበርድም ደም ተቃብቷልና::


99. ተዳፍና ስትኖር የአሥመራ እሳት

ማንም እንዳጭራት በውሃ ሲያጠፋት

በግድ አነደዱት የሸዋን ቅርጫት

ኋላ ግን ያራሉ እንደ እሳት እራት

ሸዋ ጦሩን ሰዶ አጣበት ብልሃት::


100. ተፈሪ መኮንን እንዴት ያለ ሰው ነበር?

መረታቱን ሲያውቀው እርቅ ይወድ ነበር

የወደቀው ይውደቅ ብሎ እንዲህ ሊደናገር

ምን ይበጀው ይሆን ከተማ ባላገር?

ዲንህን አጥፍተህ ዘመድክን ሳትሰትር::


101. መሸነፉን ሲያውቀው ጀግና እርቅ ይወዳል

እርቅን እምቢ ካለ አገሩ ይናዳል

ፍቹን ድረስበት እርቁ ይሻልሃል

የተፈሪ ይብቃ መዓት ይወርድብሃል::


102. መወለድ ደግ ነበር ሸዋ ጠፋ ውልድ

አስኮላ ግባ አሉት ኋላ እንዲህ ሊነድ

ልጁን መቅጣት ነበር ብልግናን ሳይለምድ

ሳዱላ አበላሽቶ ትንባሆን ሳይለምድ

ምኑ ይነወራል ሰው ቢገላምጥ፣ ቢያዋርድ

የአማራ የእስላሙን መብላት የለመደ::


103. ሐበሻ ላም ሆና ታስራ ከታለበች

ጡቷን መዥገር ወሮት ጥጃዋን ገደለች

ላምዋም ትሞታለች እየመነመነች

ወተት ቢሉ አይገኝ አንደዜ ሙታለች

ይዘገያል እንጅ ኋላ ትድናለች::


104. የሐበሻ መሬት ሌት ቀን ሲጨልም

ሐረር ወዲያ ማዶ ይፈሳል ብዙ ደም

ቂሙም አይረሳ እስከ ዘለዓለም

መንገድ ይፈልጋሉ ሐበሻን ሊቀሙ

ከስንቱ ጋር ይሆን ሐበሻ እምትገጥም?

21 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page